ከዓምናና ካቻምና በተለየ በዘንድሮው የበጋ ወቅት በየሰፈራችን ያሉት የመዋኛ ገንዳዎች ያለገደብ አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ ልጆች ያላቸው ቤተሰቦች እነዚህን የመዋኛ መዝናኛዎች ያዘወትራሉ። እርስዎም በዚህ በጋ የመዋኘት እቅድ ካለዎት ወይንም ልጆችዎን ይዘው ወደ መዋኛ ቦታዎች የሚሄዱ ከሆነ የመዋኛ ልብስ መረጣ ላይ እንዲያስቡበት ይመከራል። የአኳቲክ ሴፍቲ ከኔክሽን የሰራው ጥናት እንደሚያሳየው ሁሉም የመዋኛ ልብሶች እኩል በአይን አይታዩም ይላል። እንደ ጥናቱ ከሆነ የምንለብሰው የዋና ልብስ ቀለም የመስጠምና የመሞት አደጋን በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል ይላል። በጥናቱ እንደታየው [ከስር በምስል እንደተቀመጠው] ደማቅ ቀለም ያላቸው ብርቱካናማ ልብሶች በዋና ገንዳ ውስጥ በደንብ የሚታዩ ሲሆን ፈዛዛ ቀለም ያላቸው ልብሶች ደግሞ ብዙም አይታዩም። በዋና ገንዳዎች ሰማያዊ ወይንም አረንጓዴ ቀለም ልብሶች ለመታየት ከባድ ሲሆኑ በሀይቆችና ወንዞች ደሞ ግራጫና ነጭ ልብሶችን ለማየት አዳጋች ነው።
በመስመጥ አደጋ ጊዜ የዋና ልብስ የመታየት እድሉ ትልቅ የሆነ ልብስ ያደረገን ዋናተኛ ለማትረፍ የተሻለ እድል አለ። ለዚህም ደማቅ ቀይ ወይንም ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ልብሶች በነፍስ አድን ጠላቂ ዋናተኞች ተመራጭ ናቸው ሲል የአላይቭ ሶሉሽንስ ድረገጽ አስታውቋል።
እርስዎም በዚህ የበጋ ወቅት የመዋኘት እቅድ ካለዎት ይህን ከግንዛቤ እንዲያስገቡ ይመከራል።