
ፕሬዘደንት ትራምፕ ዛሬ በዋይት ኃውስ ሮዝ ጋርደን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለአመታት ሲበዘብዙን የነበሩ አገራት ላይ ቀረጥ በመጣል የኢኮኖሚ ነጻነታችንን እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
አሜሪካ ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ የታሪፍ ጭማሪ ያደረገችው በ1930 ሲሆን ያም በወቅቱ ታይቶ የማይታወቅ መከራ (ግሬት ዲፕሬሽን) አስከትሎ አልፏል፡፡ በበርካታ ባለሞያዎች ዘንድም በወቅቱ የነበረው ታሪፍ ለኢኮኖሚው መውደቅና ለችግሮች መራዘም አይነተኛ ምክንያት ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ፕሬዘደንት ትራምፕ በበኩላቸው አሜሪካ ከ1789 እስከ 1913 በታሪፍ ራሷን የደገፈች አገር ናት ያሉ ሲሆን ከ1913 በኋላ ለመጣው የኢኮኖሚ ድቀትና ችግሩ ሊበረታ የቻለው መንግስት ታሪፉን አጠናክሮ መቀጠል ባለመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የፕሬዘደንት ትራምፕ የታሪፍ ተመን ላይም ኢትዮጵያና ኤርትራ የተካተቱ ሲሆን ሁለቱም አገራት እያንዳንዳቸው የ10% ታሪፍ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ የ10% ታሪፍ ምን ያህል በማህበረሰባችን ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ወደፊት እንመለስበታለን፡፡