
አንዲት ኢትዮጵያ የተባለች ምሥራቅ አፍርካዊት ሀገር ለሁለተኛ ጊዜ ሊወራት የመጣውን የጣሊያን ጦር በአለም ማኅበረሰብ ፊት እንዴት ተጋፈጠች? ይሄ ሁኔታስ በወቅቱ ባሉ የህትመት መገናኛ ብዙሃን ላይ እንዴት እየተዘገበ ነው? ይህ ቲያትር ለመጀመሪያ ጊዜ በ 1930ዎቹ ሲዘጋጅ የፌደራል መንግስት የቲያትር ባለሞያዎች ስራ እንዳያጡ በሚል በተቋቋመው ዘ ሊቪንግ ኒውስ ፔፐር በተባለው ፕሮጀክት በአርተር አርንት የተዘጋጀ ነበር።
አሁን ደግሞ ኢንሲሪየስ ከጸሀፌ ተውኔት ሲቢል ሮበርትስጋ በመሆን ይሄ ሁኔታ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ባሉ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን ዘንድስ እንዴት ነው የታየው? የሚለውን ለማሳየት የ “ዘ ሊቪንግ ኒውስፔፐር”ን ገቢር ከራሳቸው ተጨማሪ ገቢር ጋር በማካተት ይህን ቲያትር አዘጋጅተዋል። ይሁን እንጂ በቲያትሩ ላይ የፕሬዝዳንት ቴዎዶር ሩዝቨልት ድምጽ እንዳይካተት እንዲያውም ቲያትሩ ከነአካቴውም እንዳይታይ ተብሎ ታገደ። አሁን ላይ ታዲያ በወቅቱ ታሪኩን የጻፉትም፣ ያገዱትም በሕይወት የሉም።

ቲያትሩ በድጋሚ በሌሎች ባለሞያዎች ከተደበቀበት ስርቻ ወጥቶና አቧራው ተራግፎ፤ ከ88 ዓመታት በኋላ ለዕይታ ሊቀርብ ነው ከተባለ በኋላ ደግሞ የፌደራል መንግስ ባወጣው አዲስ የወጪ ቅነሳ ፖሊሲ ምክንያት ይህን ቲያትር የሚያዘጋጀው ተቋም ከፌደራል መንግስት የተፈቀደለትን የ20ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ከአሜሪካ ፖሊሲጋ አብሮ አይሄድም በሚል ቲያትሩ ለህዝብ ዕይታ ለመቅረብ ሁለት ሳምንት ሲቀረው ተከልክለው የነበረ ቢሆንም “ሴቭ ኢትዮጵያ” በሚል ስያሜ በአጣዳፊ ባደረጉት የገንዘብ መዋጮ ማሰባሰቢያ አማካኝነት ከግለሰቦች በተሰበሰብው ድጋፍ ተመልሶ ወደ መድረክ መቷል። ይህ ቲያትር ለህዝብ ሊቀርብ ነው ከተባለበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጲክ ተከታዮቿ ስለ ቲያትሩ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስትጥር ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት አርብ ግንቦት 16/2025 (እ.ኤ.አ) አመሻሽ ከምሽቱ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ለዕይታ የሚቀርበውን እና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን፤ ቲያትር ለመመልከት በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው ቲያትር አሊያንስ (340 Maple Dr. SW) የተገኘነው ሁለት የኢትዮጲክ ባልደረቦች ነበርን። መሃል ዲሲ ላይ መኪና መቆሚያ መፈልግ እንዲሁም የፓርኪንግ ለመክፈል ከምንሳቀቅ ብለን ወደ ከተማዋ እምብርት የተጓዝነው በኡበር ነበር።
የደረስነው ትያትሩ ሊጀመር የደቂቃ እድሜዎች ሲቀሩት ነበር። ገና ከመግቢያው ላይ የኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ፈንዲሻ ሽታ ያውዳል። እንግዳ መቀበያውን አለፍ ብሎ በቤት ውስጥ ወደተጋረደው የቲያትሩ አዳራሽ ከመገባቱ በፊት ኢትዮጵያው ድባብ ያለው ልዩ የሆነ ጌጠኛ ምንጣፍ እና መድገፊያ ያለው ትራስ መሳይ ኢንስታሌሽን (የገጠማ ሥራ) ተብሎ የሚታወቀው የጥበብ መገለጫ ከአንስተኛ ሙዳይ እና ሀገርቤትን ከሚያስታውሱ ሰንደሎች ጋር ተቀምጦ ይታያል። በኋላ እንደተረዳነው ይሄ የማስዋብ ሥራ እንዲሁም ደግሞ በቲያትሩ ላይ የሚታዩት አባሪ የመድረክ ድምቀቶች በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኢንስታሌሽን የጥበብ ሥራ ባለሞያ ጸደይ መኮንን መዘጋጀታቸውን ተነግሯል። በኋላም ጠበብ ባለው እና ቤተሰባዊ ድባብ በነበረው አዳራሽ ውስጥ በሁለቱ ገቢሮች መሃከልም ባለሞያዋን አግኝተን ከነበረን የግል ውይይት እንደተረዳነው አግዘውኛል ካለቻቸው ባልደረቦቿ ጋር የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ችለናል።

በግምት ከ40-70 ሰው በምትይዘው የቲያትር አዳራሽ ዘልቀው ሲገቡ ታዲያ በመድረኩ ግራና ቀኝ በማዳበሪያ የተከመረው አፈር የሚነሳው ሽታ፣ የማዳበሪያው መደብ መምሰል እንዲሁም በተዘጋጀው አፈር ላይ በተለይም በገቢር ሁለት ላይ የተቀመጡት የነገስታት ምስሎች፤ እና ሙዳዮች ፣ ጨለምለም ካለው ጠባብ ክፍል ጋር ተዋህደው ሀገር ቤት ያሉ የሚመስል ድባብ እና ስሜት ይፈጥራሉ። ይሁን እንጂ መድረኩ ዝቅ ያለ እና ለተመልካች የቀረበ በመሆኑ ከፊት የተቀመጡ አንድ ተመልካች በአፈሩ ሽታ የተነሳ በንጥሻ ሲቸገሩ አስተውለናል።

በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ መምህርት በሆኑት በሲቢል ሮበርትስ አዘጋጅነት እንዲሁም ደግሞ የኢንሲሪየስ የቲያትር ቡድን ዳይሬተር በሆኑት ቲመቲ ኔልሰን የተዘጋጀው ቲያትር በተያዘለት ሰዓት የጀመረ ሲሆን፣ ሰባት ተዋኒያን ተሳትፈውበታል። ሙዚቃዊ ቲያትሩ የኦፔራ ዜማ የታጀበ፣ ከመድረኩ ግድግዳ ላይ ቃለ ተውኔቱን ተክትለው በሚለዋወጡ ታሪካዊ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ የሙሶሎኒ፣ የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ጦርነት የአየር ድብደባዎች ፣ በወቅቱ ማኅበረሰብ ላይ ያሳደሩት ጫና ምስል፣ በለንደን በዘመኑ የተካሄዱ ተቃውዎች፣ በጣሊያን የተደረጉ የድጋፍ ሰልፎች፣ በዩናይትድ ስቴትስ የጥቁር አሜሪካውያን ቁጭትና በጦርነቱ ላይ ለመሳተፍ የነበራቸውን ሚና ፤ የመገናኛ ብዙሃኑን ትኩረት በማሳየት ቲያትሩ በዚህ ዘመን ላለ ሰው በቀላሉ እንዲገባ እንዲሁም ዝግጅቱ ከሰው ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ ችለዋል።

ከሰባቱ ተዋኒያን በተጨማሪ የመድረኩ ድባብ ከልብ ሰቀላው ጋር ከፍ እና ዝቅ በሚል በፒያኖ፣ በከበሮ እና ከሀገር ከወጣ ዘመናትን ባስቆጠረው አንጋፋው ሙዚቀኛ ወረታው ውበት (በተለይም ነይ ሰንደል ገላዬ በሚለው ሙዚቃው ይታወቃል) ማሲንቆ ከሚንቆረቆር ሙዚቃ ጋር የተዋሃደ ነበር።
በገቢር አንድ በአብዛኛው የቀደመው የቲያትር አካል ሲሆን፣ ከእረፍት በኋላ ተመልሰን ስንመጣ የተመለከትነው ደግሞ በዘመን ቅብብሎሽ ውስጥ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን፣ በኢትዮጵያ ጦርነት ላይ እንደ ተስኪ ጊ ባለው የአውሮፕላን አብራሪነት፣ በሙዚቃው እንዲሁም የተለያዩ ግንኙነቶች በመፍጠር ስላደረጉት ጥረት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ስለነበራቸው የነጻነት ትግል እንዲሁም የትውልድ ቅብብሎች የታየበት ነው። ተዋኒያኑ ከሙዚቃው እና ከቃለ ተውኔቱ ጋር የነበራቸው ውህደትም የተደራሲያኑ(የተመልካችን) ልብ ሰቅዞ የሚይዝ እና በተለያየ የስሜት መዋዠቅ ውስጥ ከፍ ዝቅ የሚያደርግ ነበር።

የቲያትሩ ተዋኒያን በየመሃሉም በወቅቱ በጄኔቫ ስለነበረው የመንግስታት ውይይት፣ የሀገራት አቋም ፣ እንዲሁም በነበሩት ዓመታት ስለተከናውኑ አበይት ታሪካዊ ክስተቶች በሙዚቃ እና በስድ ንባብ ይገልጹ የነበረ ሲሆን፣ ይኸም ተመልካች ከታሪክ ፍሰቱ ሳይወጣ በቀላሉ ዘመኑን እንዲረዳ እንዲሁም የዓለም ፖለቲካን እንዲያገናዝብ ያገዘ ነበር።

ታሪኩ ሲገባደድም በወቅቱ የነበረው ትግል በዚህ መልኩ ማለፉን በማብሰር እናንተም ትግሉን ተቀበሉ የሚል አንድምታ ባለው መደምደሚያ የተጠናቀቀ ቢሆንም። ጦርነቱ ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ ዘመናትን እየጠቀሱ የሄዱት ተዋኒያን የጦርነቱ መጨረሻ ምን እንደሆነ ሳይነግሩን በእንጥልጥል ትተውናል። ይሄ ምን ልባትም ፍላጎቱ ላለው ተደራሲ ተጨማሪ እንዲመራመር ዕድሉን ቢሰጥም “ኢትዮጵያ” ሀገሪቱንም ሆነ ቲያትሩን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚያውቅ ግን የታሪክ አካሄዱን እና ዕልባቱን የሚያመላክት ነገር ቢታከልበት የሚል ስሜት ውስጥ ጥሎን እንደወጣን ቲያትሩን የታደምነው የኢትዮጲክ ባልደረቦች አውግተናል።

ሌላው የዚህ ቲያትር ድምቀት የሙዚቃ አቀናባሪዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ጀኔል ጊል አቀናባሪነት የእማሆይ ጽጌ ማሪያም ገብሩ፣ የራባይ ፎርድ (የዶ/ር አብይ ፎርድ አባት) እና የሌሎችን የሙዚቃ ሰዎችን ሥራ ያካተተው የሙዚቃ ቅንብር የዝግጅቱ ድምቀት ሆኖ አልፏል። ወደ ሦስት ሰዓት በፈጀው ቲያትር በአጠቃላይ የአዘጋጇ ጥረት፣ የተዋናዮቹ እና ዳይሬክተሩ እንዲሁም የሙዚቃ ባለሞያዎቹን እንዲሁም የመድረኩን መቼት ያስዋቡት የተለያዩ ባለሞያዎች ከፍተኛ የሆነ ሙያዊ ክህሎት የታየበት ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ ቲያትር በቀጣይ ወደ ባልቲሞር ሜሪላንድ የሚጓዝ ሲሆን ባልቲሞር በሚገኘው “ቲያትር ፕሮጀክት” በተባለው ቦታ ከሜይ 30 እስከ ጁን 1 ድረስ ይታያል። የመግቢያ ትኬቱም በዚህ ሊንክ በመሄድ ሊያገኙት ይችላሉ።