
የበጋው ወቅት መጀመሩን የሚያረጋግጠው የሜሞሪያል ዴይ በአል ዊኬንድ በርካቶች ወደ ባህር ዳርቻዎች የሚሄዱበት በአል እንደመሆኑ ከሜሪላንድና አካባቢው በርካቶች ወደ ኦሽን ሲቲ ወይንም ወደ ርሆቦት ቢች እንደሚሄዱ ይጠበቃል። የሜሪላንድ ትራንስፖርት ቢሮም በዚህ የሜሞሪያል ዴይ ዊኬንድ ከ340 ሺህ በላይ መኪኖች የቤይ ብሪጅን አቋርጠው ወደ ባህር ዳርቻዎች እንደሚሄዱ እንደሚገመት አስታውቋል።
ይህን በማስመልከትም አሽከርካሪዎች በድልድዩ ላይ የሚኖር የትራፊክ መጨናነቅን እንዴት መከላከል እንደሚቻል ባለስልጣናቱ የሚከተሉትን መልዕክቶች አስተላልፈዋል።
የትራፊክ መጨናነቅን ለማስቀረት አሽከርካሪዎች ከመደበኛው መንገድ ከዩ ኤስ 50 ውጪ ወዳሉ ሌሎች መንገዶች በመግባት ትራፊኩን ለማቋረጥ መሞከር የአካባቢው ነዋሪ ከመረበሽ ውጪ ብዙም የምታተርፉት ጊዜ ባለመኖሩ በትዕግስት በሀይ ዌዩ ላይ ሆናችሁ አሽከርክሩ ብለዋል። ይህንን የትራፊክ መጨናነቅ ለማስቀረት አይነተኛው ዘዴ የምትሄዱበትን ጊዜ መምረጥ ነው። በለሊት ወታችሁ ድልድዩን ካቋረጣችሁ አስከፊውን የቤይ ብሪጅ ትራፊክ ሳይዛችሁ ልታመልጡ ትችላላችሁ።
ሌላው በቤይ ብሪጅ ስትጓዙ ወሳኙ የቶል የመንገድ ክፍያ ነው። በዚህ መንገድ የሚጓዙ መኪኖች በኢዚ ፓስ ወይንም በታርጋቸው ወይንም በቪዲዮ-ቶል የመንገድ ክፍያቸውን ይፈጽማሉ። ከሁሉም ርካሹ በኢዚ ፓስ እንደሆነና ኢዚ ፓስ የሌላቸው ሰዎች በዚህ ሊንክ ሄደው አካውንት መክፈትና የኢዚ ፓስ መቆጣጠሪያ መሳሪያውን መግዛት ይችላሉ።
አሽከርካሪዎች በተጨማሪም የመስመር መቆጣጠሪያዎችን እንዲያስተውሉ፤ ዝግ ብለው እንዲጓዙ፤ ከተወሰነው የፍጥነት ወሰን በላይ እንዳይጓዙ፤ ተመክሯል።
የሜሪላንድ ስቴትም ፖሊሶቹን አሰማርቶ ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚያሽከረክሩ፤ ጠጥተው የሚያሽከረክሩና ሌሎች ሞገደኛ አሽከርካሪዎች እንደሚይዝና አስፈላጊውን ቅጣት እንደሚጥል አስታውቋል። አሽከርካሪዎችም በመንገድ ላይ አደጋ ካዩ ወይንም ለአደጋ የሚያጋልጥ አደገኛ ባህርይ ያለው አሽከርካሪ ካዩ 9-1-1 ላይ ወይንም ለሜሪላንድ ፖሊስ ዲስፓች በ410-537-7911 በመደወል ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉ ተነግሯል።