
የባይደን ቢሮ ዕሁድ ሜይ 18 2025 ባወጣው መግለጫ የቀድሞው ፕሬዘድነት በአስከፊ የፕሮስቲት ካንሰር እንደተጠቁና ይህ ካንሰርም ወደ አጥንታቸው እንደተስፋፋ አስታውቀዋል። በመግለጫው አክለውም ይህ የካንሰር አይነት በሆርሞን ለሚደረግ ህክምና ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ህክምናው ተስፋ እንዲኖረው ያደርጋል ብለዋል።
ይህን ዜና ተከትሎም ፕሬዘደንት ትራምፕ ለባለቤታቸው ለጂል ባይደን የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን ልከዋል።
የቀድሞው ምክትል ፕሬዘደንት ካማላ ሀሪስና ባለቤታቸው ዳግ ኢምሆፍም በበኩላቸው ፕሬዘደንት ባይደንን፤ ባለቤታቸውን ዶክተር ጂል ባይደንንና መላው ቤተሰቦቻቸውን በጸሎታቸው እንደሚያስቧቸው በማህበራዊ ድረገጽ አካውንታቸው ላይ አስታውቀዋል።
ጣልያን ከነበራቸው የስራ ጉብኝት የተመለሱት የአሁኑ ምክትል ፕሬዘደንት ጄዲ ቫንስም በበኩላቸው ለቀድሞ ፕሬዘደንታችን መልካም ጤንነት እንደሚመኙና ከዚህ ህመም በቶሎ እንደሚድኑ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ጄዲ ቫንስ አክለውም የቀድሞው ፕሬዘደንት ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ጤናማ እንዳልነበሩ እንደሚያምኑና ሀቀኛ የሆነ ምላሽ ለአሜሪካን ህዝብ እንደሚያስፈልገው የተናገሩ ሲሆን በዙሪያቸው የነበሩ ሰዎች ህመማቸውን ደብቀው አገር ያስተዳድሩ እንደነበርና ይህ ትክክል እንዳልነበር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከነዚህ በተጨማሪም የቀድሞ ፕሬዘደንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ በርካቶች ለጆ ባይደንና ለቤተሰባቸው መልካም ምኞታቸውን ልከዋል።