ሐሙስ ኦክቶበር 31 2024 የፕሪንስ ጆርጅ ካውንቲ ኤክስኪውቲቭና ዴሞክራትን ወክለው በዩናይድ ስቴትስ ሴኔት ሜሪላንድን ወክለው ለመመረጥ ቅስቀሳ እያደረጉ የሚገኙትን አንጀላ ኦልሶብሩክስን በሪቨርታውን ኮመንስ ማርኬትፕሌስ ጎዳናዎች ላይ ከበጎ ፈቃደኛ ደጋፊዎቻቸውጋ በመሆን የምረጡኝ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ ታድመናል። ከቅስቀሳቸው በኋለም ጥቂት ደቂቃዎችን ለኢትዮጲክ ባልደረባ ቃለመጠይቅ ፈቅደው ከፍትህ እስከ የስደተኞች ጉዳይ እንዲሁም ውጭጉዳይ ፖሊሲ እና በርካታ ሌሎች ከአንባቢዎች የወሰድናቸውን ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሻቸውን ሰተውናል።
በተለያዩ ሚዲያዎች እንደሚነገረው ይህ የሜሪላንድ የሴኔት ፉክክር በመጪው አመት የትኛው ፓርቲ በሴኔት የበላይነትን እንደሚይዝ የሚወስን ትልቅ ፋይዳ ያለው ውድድር እንደሆን ይታመናል።
ኦልሶብሩክ ስለ ማህበረሰባዊ ፍትህና ኢኮኖሚ
ማህበረሰባዊ ፍትህንና ኢኮኖሚን በሚመለከት አንጀላ ኦልሶብሩክስ ያላቸውን ቁርጠኝነት በተለይም ደህንነታቸው በተጠበቁ አካባቢዎች ላይ መኖር እና የተሻለ የኢኮኖሚ ደህንነትን መፍጠር ላይ እንደሚሰሩ እስካሁንም በነዚህ ጉዳዮች በካውንቲያቸው ትልቅ ስኬት እንዳስመዘገቡ ገልጸው ወደሴኔት ሲሄዱም ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
የስደተኞች ህግና የኢሚግሬሽን ቢሮ አሰራር መጓተት
የስደተኞች ህግና የኢሚግሬሽን ቢሮ አሰራር መጓተትን በሚመለከት ኦልሶብሩክስ በዩናይትድ ስቴትስ ኢሚግሬሽን ቢሮ የሚታየው መጓተት መፍትሄ እንደሚያሻውና ይህንንና የህገወጥ ፍልሰተኞችን ማስቀረት በምንችልባቸው ጉዳዮች ላይ ከማናቸውም ፓርቲ ያልወገኑ ህጎች እንዲጸድቁ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል። በተለይም በህጋዊ መንገድ አገር ውስጥ የገቡ በቶሉ ጉዳያቸውን እንዲጨርሱና ዜጋ የሚሆኑበት መንገድ እንዲመቻች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች
ስለኢትዮጵያ በተለይም በቅርቡ አምነስቲና የዩናይትድ ስቴትስ ስቴት ዲፓርትመንት ባወጡት መግለጫ ላይ መንግስታዊ አካላት ስለሚያደርሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለጠየቅናቸው ጥያቄ ኦልሶብሩክስ ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች በአሜሪካ ፖለቲካ ያላቸውን ትልቅ ቦታ በማስረዳት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም ዙሪያ ዴሞክራሲ እንዲንሰራፋ ሰብዓዊ መብቶችም እንዲከበሩ ዩናይትድ ስቴትስ እንደምትደግፍ ተናግረዋል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከትም እንደተባበሩት መንግስታት ካሉ ተቋማትጋ ነጻነትንንና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚሰሩ ወገኖችን እንደሚደግፉም ተናግረዋ።
ከትምህርትጋ በተያያዘ የወላጆች መብትን ማክበርንና መተማመንን መፍጠር
ተፎካካሪዋ የወላጆች ችግር በተለይም ከእምነታቸውጋ በሚጋጩ ጉዳዮች ዙሪያ ወላጆች ድምጽ ሊኖራቸው እንደሚገባ እንደሚያምኑና እሳቸውም የ19 ዓመት ታዳጊ ወላጅ እንደመሆናቸው የወላጆች ስሜት እንደሚገባቸው የጠቆሙ ሲሆን አክለውም ወላጆች በልጆቻቸው ትምህርት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሀሳብ መስጠት እንደሚገባቸው ግን ይህ የሴኔት አባላት ሀላፊነት እንዳልሆነ ይልቅስ የአካባቢው የትምህርት ቦርድና የትምህርት ቤቶቹ ውሳኔ እንደሚሆን ገልጸው እሳቸው በሚችሉት የህዝብ ትምህርት ቤቶች በደንብ እንዲደራጁ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ኦልሶብሩክስ ለፕሪንስጆርጅ ካውንቲ የኢኮኖሚ እድገት በተለይም የኤፍ ቢ አይ ዋና መስሪያ ቤት ወደዛ እንዲዛወር በሰሩት ስራ እንደሚኮሩና ይህ በሺዎች የሚቆጠር የስራ ዕድል እንዳመጣ ገልጸዋል። አክለውም ለአካባቢያዊ ዜና ተቋማት ድጋፋቸውን እንደሚለግሱ ጠቁመዋል።
ስለሚወዱት የኢትዮጵያ ምግብ ወይንም ሙዚቃ ጠይቀናቸው ምርጫቸው ቡና እንደሆነ ነግረውን ሲያበቁ የኢትዮጵያና የኤርትራ ማህበረሰብ ሀይማኖተኞችና ለዕምነታቸው አዳሪ መሆናቸውን እንደሚወዱላቸውና እሳቸውም አማኝ እንደመሆናቸው ከኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጓደኞቻቸውጋ በየዕምነት ተቋማቱ ሄደው ያዩትን መንፈሳዊነት እንደሚወዱት ተናግረዋል።
አንጀላ ኦልሶብሩክስና ደጋፊዎቻቸው ከኢትዮጲክጋ ከነበራቸው ቃለ መጠይቅ በኋላ በቢሯቸው በቀድሞው ፕሬዘደንት ባራክ ኦባማ ድንገተኛ የማበረታቻ ጉብኝት ተደርጎላቸዋል። ፕሬዘደንት ኦባማ በጉብኝታቸው ወቅትም አንጀላ ኦልሶብሩክን በመምረጥ ዴሞክራቶች የሴኔት የበላይነታቸውን አስጠብቀው እንዲቀጥሉ ማድረግ እንደሚገባና ይህም ለካማላ ሀሪስ ስራዋን እንድታከናውን የሴኔት የበላይነት ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል። አክለውም “ሁሉም ሜሪላንዳዊ መራጭ ወቶ መምረጥ አለበት፡ ለወዳጅ ጓደኞቻችሁ ንገሯቸው …ይህንን ተቀምጠን ማሳለፍ አንችልም” ሲሉ ተደምጠዋል።
☝🏾☝🏾Top: Image Credit: Alsobrooks for U.S. Senate
ሙሉ ቃለመጠይቁን ለማየት ቪዲዮን ከስር ይመልከቱ