የቨርጂንያ ገቨርነር ግሌን ያንኪን በቅርቡ በዲ ኤም ቪ ፋይላቸው ላይ የዜግነት መረጃቸው በአግባቡ አልተካተተም ወይንም ዜግነታቸው አልተረጋገጠም ባሏቸው ከ1600 በላይ በሆኑ የቨርጂንያ ነዋሪዎችን ህጋዊ የመምረጥ መብት እንዲገፈፍ አድርገው ነበር።ይህም የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች በምርጫ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ከተጓዟቸው መንገዶች አንዱ ቢሆንም በርካቶች ዜጎች በዚህ ህግ ሰለባ እንደሆኑ ተነግሯል።
ይህን ጉዳይ ወደፍርድ ቤት የወሰዱት የቨርጂንያ ኮአሊሽን ፎር ኢሚግራንት ራይት፤ ዘ ሊግ ኦፍ ውሜን ቮተርስ ኦፍ ቨርጂንያና የአፍሪካን ኮሚውኒቲስ ቱጌዘር የተባሉት ተቋማት ታዲያ በጊዜያዊነት በአካባቢያዊ ፍርድቤቶች ውሳንኔውን ማሳገድ ችለው የነበረ ቢሆንም ኦክቶበር 30 የተሰየመው ሱፕሪም ኮርት የያንኪንን ይግባኝ በመደገፍ ውሳኔ ሰቷል።
ይህንን ተከትሎም የአፍሪካን ኮሚውኒቲስ ቱጌዘርን ወክለው የፕሬስ መግለጫ የሰጡት አቶ ሰለሞን አያሌው ተቋማቸው አሁንም ቢሆን ለመራጮች መብ በተለይም የአሜሪካ ዜግነት ኖሯቸው የመምረጥ መብታቸውን ለተገፈፉ ሰዎች እንደሚታገሉና በዚህ ሲስተሚክ ህግ ለተጎዱ ዜጎች ድምጻቸው እንዲሰማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የቨርጂንያ ስደተኞች መብት ቅንጅት ተወካይ የሆኑት ሞኒካ ሳርሚየንቶ በበኩላቸው መምረጥ የዩናይትድ ስቴትስ ትልቁና ዋነኛው መብት እንደሆነና ገቨርነር ያንኪንና አቶርኒ ጀነራል ሚያሬዝ ተግባራዊ ያረጉት ህግ ናቹራላይዝድ ዜጎችንና እዚህ የተወለዱ ዜጎችን ከምርጫ የሚያገል ህግ ነው ብለዋል።
በመግለጫቸው አክለውም በቨርጂንያ ህግ መሰረት ማንኛውም ሰው በምርጫው ዕለት በምርጫ ቦታ በመገኘት ተመዝግበው ድምጻቸውን መስጠት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ላይ ደብሊው ቲ ኦ ፒ ያናገራቸው ግሌን ያንኪን ይህ ለህገመንግስቱና መደበኛ መረዳት (Common Sense) ላለው ሰው ድል ነው ብለዋል። አክለውም ማንኛውም አሜሪአክዊ የሆነና በምርጫ እንዲሳተፍ ህጉ የሚፈቅድለት ሰው በሙሉ በምርጫው ቀን እዛው ተመዝግቦ መምረጥ እንደሚችልም አክለው ተናግረዋል።