በጁላይ 2024 በቀረበው የበጀት ረቂቅ ዋሽንግተን ዲሲ በአንድ ጉዞ 1$ ብቻ እያስከፈለ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውን የሰርኩሌተር የባስ አገልግሎት እንዲቋረጥ ወስነው ነበር፡፡ የዲሲ ሰርኩሌተር ከዲሲ መንግስት በተበጀተለት ገንዘብ የሚተዳደር ተቋም እንደመሆኑ የዲሲ መንግስት በጀቱን ሲያቋርጥ በአመቱ መጨረሻ በተቋሙ በተለያየ ዘርፍ ይሰሩ የነበሩ 276 ሰራተኞች ከስራቸው ይፈናቀላሉ፡፡
በ2023 የበጀት አመት የዲሲ ሰርኩሌተር ባስ አገልግሎት የ31ሚልየን ዶላር በጀት የነበረው ሲሆን በ2024 የበጀት አመት ደሞ የ37.7 ሚልየን ዶላር በጀት ተመድቦለት ነበር፡፡ ሆኖም በ2025 የበጀት አመት ይህ አገልግሎት በመቋረጡ የባስ አገልግሎት የሚከተሉት የባስ መስመሮች ከኦክቶበር ጀምሮ እንዲቋረጡ ተወስኖባቸዋል፡፡
- ሮዝሊንና ዱፖንት ሰርክል መስመር ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ
- በውድሊ ፓርክና አዳምስ ሞርጋን እንዲሁም በጆርጅታውንና ዩኒየን ስቴሽን መሀል የነበሩ የምሽት አገልግሎቶች እንዲቋረጡ
- የተቀሩት መስመሮች ቀድሞ ከነበረው በየ10 ደቂቃው የሚሰጡት አገልግሎት በእጥፍ አድጎ በየ20 ደቂቃው ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ
- እንዲሁም በዉድሊ ፓርክና አዳምስ ሞርጋን፣ በጆርጅታውንና ዩኒየን ስቴሽን፤ በኮንግረስ ሄይትስና ዩኒየን ስቴሽን፣ እና በኢስተርን ማርኬትና ለንፋንት ፕላዛ አገልግሎት የሚሰጡት ባሶች እንደወትሮው እስከ እኩለ ለሊት ሳይሆን አገልግሎታቸውን በጊዜ ምሽት 9pm ላይ እንዲያተናቅቁ ተወስኖባቸዋል፡፡
- የናሽናል ሞል መስመር ደሞ ሁሌም ምሽት 7pm ላይ አገልግሎት እንዲያጠናቅቅ ተወስኖበታል፡፡
የዲሲ ሰርኩሌተር የባስ አገልግሎት ከ2005 ጀምሮ ለዲሲ ነዋሪዎችና ጎብኚዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ባለፈው አመት ብቻል ለ1.9 ተገልጋዮች የትራንስፖርት አገልግሎት ሰቷል፡፡
የዲሲ ሰርኩሌተር በዲሴምበር 31 በሚቋረጥበት ወቅት የሚኖሩ መስተጓገሎችን ለመሸፈን የዲሲ ሜትሮ ባስ ተጨማሪ ባሶችን በመመደብ አገልግሎት ለመስጠትና ጉድለቱን ለመሸፈን እንደሚሞክር የዲሲ ትራንስፖርቴ ቢሮ ሃላፊ ሻረን ኪርሽባም በኦክቶበር መጀመሪያ አስታውቀው ነበር፡፡
ምንም እንኳ የተወሰኑ የሰርኩሌተር ሰራተኞች በዲሲ ሜትሮ ባለስልጣን (ዋሽንግተር ሜትሮፖሊታን ኤርያ ትራንዚት ኦቶሪቲ) ተለዋጭ ስራ ቢያገኙም እንደአዲስ ተቀጣሪ ስራ የሚጀምሩ በመሆኑ በርካት ጥቅማጥቅሞችና ያካበቱት እድገት በዜሮ ተባዝቶ እንደ አዲስ አንደሚጀምሩና ይህም ህይወታቸውን እንደሚያከብደው ተነግሯል፡፡ የተቀሩት ሰራተኞች እጣፈንታ ደሞ ስራ አጥነት እንደሆነና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሰራተኞቹ የህብረት ስራ ማህበር አስታውቋል። የህብረት ስራ ማህበሩ የከንቲባዋን ድንገተኛ ውሳኔም ተቃውሟል፡፡ እንደ ህብረት ስራ ማህበሩ ከሆነ ሰራተኞቹ እስከ 2028 የሚያዘልቃቸው የ5 አመት ይስራ ኮንትራት ውል የፈጽሙ ቢሆንም የዲሲ ከንቲባ በድንገት ኮንትራታቸውን ማቋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡
የዲሲ ካውንስል ታዲያ እኚህን ጨረቃ ላይ የቀሩ ሰራተኞች ለማገዝ በሚል የዲሲ ሰርኩሌተር ባሶችና ማናቸው ንብረት ተሸጠው የሚገኘው ገቢ በሙሉ ለነዚህ ሰራተኞች እንዲሰጥ የሚያዝ ህግ በሙሉ ድምጽ አሳልፈ የነበረ ሲሆን የዲሲ ከንቲባ ኝ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው ኦክቶበር 23 2024 ባወጡት ደብዳቤ ሽረውታል፡፡
ከንቲባዋ በደብዳቤው የካውንስሉ ውሳኔ ለኮንትራት ሰራተኞች አዲስ መስፈርት እንደማውጣት እንደሆነና ይህ ህግ ለሁሉም የመንግስት ኮንትራክተሮች ተፈጻሚ እንዲሆን ከተደረገ ከገንዘብ አኳያ አዋጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡
የካውንስል አባላቱ በተለይም ፊል ሜንደልሰንና ቻርለስ አለን በከንቲባዋ ተቃራኒ በመቆም የከንቲባዋን ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንደማይቀበሉና ባጸደቁት ህግ መሰረት ከባሶቹና ሌሎች ንብረቶች የሚገኘውን ሽያጭ ለሰራተኞቹ እንዲደርስ እንደሚሰሩ አሳውቀዋል፡፡ የዋርድ 6 ካውንስል አባል የሆኑት ቻርለስ አለንም በትዊተር ገጻቸው የከንቲባዋን ውሳኔ እንደማይቀበሉትና ተቀናሽ ሰራተኞች መደገፍ እንዳለባቸው ትላንት ማክሰኞ ኦክቶበር 29 2024 በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡