እንደ ዊኪፒዲያ መረጃ ከአውሮፓውያን ወረራ በፊት የቦልቲሞር አካባቢ ሳስኩዌሃኖክ ለተባሉ ኔቲቭ አሜሪካውያን የአደን ቦታ ነበር። በኋላ ላይም በ1706 የአዎሮፓ ቅኝ ገዢዎች የሲጋራ/ትምባሆ ንግዳቸውን ለማቀላጠፍ የቦልቲሞር ወደብን መሰረቱ። የቦልቲሞር ከተማም የወደቡን መመስረት ተከትሎ በ1729 ተመሰረተ።
በ1812 ዓ.ም የነበረውና የቦልቲሞር ውጊያ (Battle of Baltimore) የሚባለው ጦርነት ላይ የእንግሊዝ ጦር ፎርት ማክሄንሪ የተባለውን ምሽግ ለመጣስ ሞክሮ ተሸንፎበታል።
በዚህ ወቅት ነው ፍራንሲስ ስካት ኪይ የተባለው ሰው “ስታር ስፓንግልድ ባነር” የተሰኘ ግጥም የፃፈው። ይህም ግጥም በኋላ ላይ በ1931 የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙር ሆኖ እስካሁን እያገለገለ ይገኛል።
ቦልቲሞር በርካታ በቅርስነት የተመዘገቡ ሰፎሮች አሏት። ከነዚህም ውስጥ በቅርብ የተካተቱት ፌልስ ፖይንት፤ ፌደራል ሂልና ማውንት ቨርነን ይገኙበታል።
ከዲሲ 35 ማይል ላይ የሚገኘው ቦልቲሞር እንደትራፊኩ ሁኔታ መንገዱ ከ45-60 ደቂቃ ይፈጃል ። እዛ ከደረሱ በኋላ መኪና ማቆምሚያ ለማግኘት ትንሽ መሽከርከር ሊኖርብዎ ይሆናል። እኛ የአኳሪየም ሜምበርሺፓችን የ25% ዲስካውንት ስላለው አኳሪየም አካባቢ የነበሩትን የፓርኪንግ ጋራጆች ነው የተጠቀምነው። ለሙሉ ቀን 16 ብር ከፍለናል።
ኢነር ኃርበር
ኢነር ሃርበሩ ላይ የእግር ጉዞ በማድረግ ከስር የተዘረዘሩት አብዛኞቹ ቦታዎች መጎብኝተ ይቻላል። ኢነር ኃርበር ላይ ያሉትን ቦታዎች ለማየት መኪና ብዙም አያስፈልግም። ሙሉውን ግን መጨረስ የሚታሰብ አይደለም ምክንያቱም 7 ማይል ላይ የተዘረጋ መንገድ ነው።
ወርልድ ትሬድ ሴንተር
ወደ ህንፃው ከመግባትዎ በፊት በኒውዮርክ በአውሮፕላን ተመተው የወደቁት መንትያ ህንፃዎች ስብርባሪ የተሰራ መታሰቢያ ከህንፃው ፊት ለፊት ያገኛሉ።
መግቢያው ለአዋቂ 8$ ለልጆች ደሞ 5$ ነው። ከልጆቻችሁ ጋር ከሆነ የምትሄዱት በጣም ይደሰቱበታል። ከ27ኛ ፎቅ ላይ ከተማውን በሙሉ ማየት እንዲችሉ ሆኖ የተሰራ መቃኛ ማማ ነው። ዙሪያውን በ4ቱም አቅጣጫ ከተማውን ማየት ይችላሉ። በተጨማሪም 25 ሳንቲም እየተጨመረበት የሚሰራው አቅርቦ ማያ መነፅር ስላለ በጣም ሩቅ ያሉ የከተማውን ክፍሎች በደንብ ማየት ይቻላል። ልጆቻችን ወደውታል።
ኮስት ጋርድ የመርከብ ሙዚየም
ይህ የመርከብ ሙዜየም ነው። ልጆቻችን ከዚህ በፊት መርከብ ውስጥ ገብተው ስለማያውቁ እንዲያዩት ብለን ነው የገባነው። ይህ የኮስት ጋርድ መርከብ ሁሉም የተሟላለት መርከብ ነው። ልጆቻችን ብዙም የተዝናኑ አይመስለንም። ለኛ ግን ግሩም ነበር።
አኳሪየም – 4ዲ
ቦልቲሞር ከሄዳችሁ አኳሪየሙን ሳትጎበኙ ባትመለሱ እንመክራለን። መዓት አይነት የውኃ እንሣት በጣም ውብና ለፎቶ በሚያማምሩ መስታወቶች ታያላችሁ። ልጆቻችሁ ስለ ማሪን ላይፍ ብዙ ይማራሉ። እኛ እዚህ ምንም የምንላችሁ ነገር አይኖርም ምክንያቱም እዚህ መዘርዘር ከምንችለው በላይ የሚታዩ ነገሮች አሉ። አኳሪየሙን የምትጎበኙ ከሆነ ደሞ አመታዊ ሜምበርሺፑን ብትገዙ የሚሻል ይመስለናል። ምክንያቱም ለአንድ ሰው ለአንድ ቀን መግቢያ $39.95 ለልጆች 29.95$ ሲሆን ሁለት ልጆች ላሉት ቤተሰብ በጠቅላላ በአንድ ጉዞ 139.8$ ይከፍላሉ። አመታዊ አባልነትለአንድ ሰው 75$ ሲሆን ለቤተሰብ (2 አዋቂና 4 ልጆች) 195$ ነው። በአመት ሁለቴ ከሄዳችሁ ዋናችሁን ትመልሳላችሁ። ሶስተኛው ትርፍ ነው ማለት ነው። እኛ እስካሁን ሁለቴ ሄደናል። ሁለቱንም ትሪፕ ልጆቻችን ወደውታል። በዛ ላይ ብዙ ያላየናቸው ቦታዎች ስላሉ ገና እንሄዳለን። ከምንም በላይ ደግሞ ወደ አኳሪየም ለመግባት ያለውን ረጃጅም ሰልፎች ሜምበር ስትሆኑ እናንተን አይመለከቱም። የሜምበር’ስ ብቻ መግቢያ በር አለ። እኛ የሄድን ቀን የነበረው ሰልፍ ቢያንስ 30 ደቂቃ ያስጠብቀን ነበር በሜምበር መግቢያ ባያስቀድሙን።
ሌላው አኳሬየም ከደረሳችሁ 4D ሲኒማውን ግቡ። ለሜምበር ዲስካውንት አለው፡፡ 20$ የነበረውን መግቢያ ለ 4 ሰው 16$ ነው የከፈልነው። የ15 ደቂቃ ፊልም ቢሆንም ልጆቻችንን ልባቸው እስኪዎልቅ ነው ሲስቁ የነበረው።
ሊትል ኢታሊ 1-ምሳ
በሁለቱም ዙር የጎበኘነው ሌላው ሰፈር ሊትል ኢታሊ ነው። እንደኛ ምግብ ወዳጆች ከሆናችሁ እዛ ካሉት በርካታ ትንንሽ ምግብ ቤቶች በአንዱ አንጀት የሚያርስ ምግብ መመገብ ትችላላችሁ። እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሄድ ሳባቲኖ’ስ በአሁኑ ደሞ አሚቺ’ስ የተባሉ ቦታዎች ምሳችንን በልተናል። በአሁኑ ዙር አሚቺ’ስ ከነልጆቻችን 4 ምግብ አዘን ቲፑን ሳይጨምር $78 ብር ከፍለናል። ምግቡ በጣም አሪፍ ነው ግን ያጠፋነው 4 ሙሉ ምግብ ማዘዛችን ነው። ለሙሉ ቤተሰቡ 2 ወይም 3 ምግብ በቂ ነው። እና ደሞ… ወደ አኳሪየም ከመግባታችሁ በፊት ምግብ ብሉ። ልጆቻችሁም እናንተም ስለ ረኃብ ሳታስቡ አኳሪየሙን ትዝናናላችሁ። ከምንም በላይ ግን ሊትል ኢታሊ ትንሽ ሰፈርና፤ ጠባብ መንገዶችና ዶሮ ማነቂያን የመሰለ ቫይብ ያላት ሰፈር ከመሆኗ በላይ ምግብ ቤቶቿም የፒያሳን ኤንሪኮ መደዳ ወይንም በመሀሙድ ሙዚቃ ቤት ወደታች ያሉ ምግብ ቤቶችን ያስታውሳል።
ሊትል ኢታሊ 2 – ቫካሮ
ሊትል ኢታሊ ከገባችሁ የቫካሮ ኬኮችን ሳትሞክሩ እንዳትመለሱ። አይስክሬም የመጨረሻ ትንሹን እዘዙ። በሳላድ ባወል ነው የሚቀርብላችሁ። የእኛ ፌቭ የነበረውን ኤክሌር አዘን እሩቡን መጨረስ አቅቶን አስጠቅልለነው ይኸው እስካሁን አለ። ግን በጣም አሪፍ አሪፍ ኬኮችና ኩኪዎች አሉ።
ፓይረት ጀልባ
ልጆች ቢኖሯችሁም ባይኖሯችሁም እነዚህን በባትሪ የሚሰሩ ጀልባዎች ሞክሯቸው። አሪፍ ኤክስፒሪያንስ ናቸው። ለ4 ሰዎች (ሙሉ ቤተሰብ) 30$ ነው ለ 30 ደቂቃ። በጣም አሪፉ ነገር ጀልባውን ራሳችሁ ናችሁ የምትሾፍሩት። አብሯችሁ የሚሳፈር ሰራተኛ የለም። እንዴት እንደምትነዱ ያሳያችኋል ከዛ ይዛችሁ መዞር ነው።
ሌክዚንግተን ማርኬት
ከቦልቲሞር ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ ራሱ ጥንታዊው የገበያ ቦታ ነው። በአሁኑ ሰዓት $40 ሚልየን በሚደርስ ወጪ እድሳትና ሪሞዴሊንግ እየተደረገለት ሲሆን 40 የሚደርሱ መግብና ጣፋጮች የሚሸጡ የንግድ ተቋማት በውስጡ አሉ።
ከላይ ከጠቀስናቸው በላይ በጣም ብዙ ፕሌይግራውንዶችና ሌሎች መዝናኛዎችም አሉ። እነዚህ እኛ ከሰሞኑ በአንድ ቀን ጉዞ ያየናቸው ቦታዎች ናቸው። ቦልቲሞር ግን በውስጡ በርካታ ሌሎች የሚጎበኙ ቦታዎች አሉት። በቀጣይም እንዲሁ ሄደን ሌሎች ያላየናቸውን በተለይ ሙዚየሞቹን፤ ጋለሪዎቹንና ሌሎችንም ለማየት እቅድ አለን። እንደተለመደው ያየነውን እናጋራችኋለን።