ከአቶ ማርክ ኤልሪችጋ ያደረግነው ቆይታ ትራንስክሪፕት እነሆ .. ቪዲዮው ከስር መጨረሻ ላይ አለ።
ራስዎን ያስተዋውቁልን
ማርክ ኤልሪች እባላለሁ.. የሞንጎምሪ ካውንቲ ኤክስኪውቲቭ ነኝ። በዚህ ቦታ ላይ ላለፉት 3 አመት ተኩል ሳገለግል ቆይቻለሁ። ከዛ በፊት ለ12 አመት የሞንጎምሪ ካውንቲ ካውንስል አባል ነበርኩ። በተጨማሪም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አስተማና የታኮማ ፓርክ ከተማ ካውንስል አባል ሆኜ አገልግአለሁ። በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመኔ ለሁሉም ሰው የተሻለ ነገር ለመፍጠር የተቻለኝን አድርጌያለሁ። እያደረግሁም ነው።
በስራዎ ያጋጠመዎት ትልቁ ፈተና ምን ነበር?
ትልቁ ፈተና ኮቪድ ነበር። የአመት በጀቴን አዘጋጅቼ ያቀረብኩ ቀን በኮቪድ ምክንያት ሁሉም ነገር ተዘጋ። ካውንስሉም ያቀረብኩትን ረቂቅ በጀት ሊያፀድቅልኝ አልፈለገም። ባለፈውም አመት እንዲሁ ተመሳሳይ በጀት ነው የነበረን። የገንዘብ እጥረትና ኮቪድ ያሰብናቸን የልማት ስራዎች እንዳናሳካ ትልቅ እንቅፋት ነበሩ። ባለፈው አመት ዳዲስ ነገሮችን በካውንቲው ለማስጀመር አስበን ሆኖም በቂ ገንዘብና አቅም ባለመኖሩ ሳናሳካ ቀርተናል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ዘንድሮ ልናስገባ ያቀድነውን ገንዘብ አስገብተናል። ባንኮች የያዙልንን የመጠባበቂያ በጀት አሟልተናል፡፤ የጡረታ ገንዘብ ወደነበረበት ተመልሷል፤ እናም ዘንደሮ ገቢያችን በማደጉ ከቀድሞው የተሻለ በጀት አቅምን ላገናዘቡ መኖሪያ ቤቶች (Affordable Housing)፤ ለልጆች እንክብካቤና ትምህርት ተመድቧል።
ኢኮኖሚውን ለማሻሻልና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ ምን ሊሰሩ አስበዋል?
ካውንቲው የራሱንና ከፌደራል መንግስት ያገኘውን ድጎማ አጣምሮ ለድንገተኛ ጊዜ በመጠባበቂያነት ከተያዘው በጀት ላይ ለነዋሪዎቹ ድጎማ ያደርጋል። ልምሳሌ በአሁኑ ሰዓት የቤት ኪራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ነዋሪዎች የቤት ኪራይና የመብራትና ውኃ ቢ ክፍያ ድጋፍ እያደረግን ነው። ይህን ድጋፍ ለሁሉም ማድረስ ስለማይቻል ቅድሚያ ገቢያቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ነዋሪዎች ብቻ ነው የሚደረገው። እንዲሁ በተመሳሳይ ወደስራ ላልተመለሱና የምግብ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ማንኛውም ነዋሪዎች ከመጠባበቂያ በጀት ላይ ልክ በኮቪድ ጊዜ እንደነበረው የምግብ ድጋፍ ይደረጋል። እንዚህ በዋናነት የቤት ኪራይ ድጋፍና የምግብ ድጋፍ ዋናዎቹ ሲሆኑ የማህበረሰብ የጤና ክሊኒኮች ደሞ በዋናነት ኢንሹራንስ ለሌላቸው ነዋሪዎች የጤና እንክብካቤ ያደርጋሉ። ክትባቶችንም በነፃ ያቀርባሉ። በተለይም ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑና መጓጓዣ መኪና የሌላቸው ሰዎች እንዳይቸገሩ በየአቅራቢያቸው ክትባቶችን ተደራሽ አድርገናል። በካውንቲው ካሉ እንደ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ያሉ ጋር ጥሩ ትብብር አለን። ይህም ስለካውንቲው ነዋሪዎች የተሻለ መረዳት እንዲኖረን አግዞናል።
በመንግስትና በማህበረሰቡ መኃል ያለውን የቋንቋ ክፍተት ለማጥበብ ምን ሊሰሩ አስበዋል?
እስካሁን ስናረገው እንደነበረው ሰዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋን እንዲማሩ እናመቻቻለን። በዚህም የጊልክሪስት ማዕከል ዋና ተጠቃሽ ነው። በዊተንም ቢሮ አላቸው። በተጨማሪም በርካታ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች የቋንቋ ትምህርት አገልግሎት እንዲያቀርቡ ገንዘብ እንለግሳለን። በቀጠይም እነዚህ ፕሮግራሞች በዘላቂነት እንዲቀጥሉ የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የአንድ ሰው ስኬት በዋናነት ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለው የመግባባት ችሎታ ላይ የተመረኮዘ ነው። ለዛም ነው ነዋሪዎቻችን ስኬታማ እንዲሆኑ የቋንቋ ትምህርትና ተግባቦት ስልጠናዎች ላይ ድጋፍ የምናደርገው።
ለቀጣይ ከተመረጡ ለአካል ጉዳተኞች ልጆችና ለወላጆቻቸው እስካሁን ካለው ተጨማሪ ምን ለማድረግ አስበዋል?
ከአካል ጉዳት ጋር በተገናኘ መገለል የኢትዮጵያውያን ኮሚውኒቲ ብቻ ችግር አይደለም። በርካታ ወላጆች በዚህ ይቸገራሉ። የካውንቲው ትምህርት ቤቶች በተለይም ለህፃናት የተዘጋጁ በርካታ አካታች ፕሮግራሞች አሏቸው። በተጨማሪም በርካታ ለትርፍ ላልተቋቋሙ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እናደርጋለን። በተጨማሪም በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች አገልግሎቶቻቸው ተደራሽ እንዲሆኑ እንደ ስፓኒሽ፤ አማርኛ ቻይኒኛና በመሳሰሉ ቋንቋዎች ተገልጋዮችን ያስተናግዳሉ። በተጨማሪም ወላጆች እነዚህን ድርጅቶች ላይ እምነት እንዲኖራቸውና ያልምንም ስጋት ልጆቻቸውን ይዘው መምጣት እንዲችሉ እንሰራለን። እንዳልኩት ይህ ችግር የኢትዮጵያውያን ብቻ ችግር አይደለም። እነዚህ ሰዎች ወደፊትም አይመጡም፤ እርዳታም አይጠይቁም። ሁሉም ማህበረሰብ በውስጡ እንዲህ ያሉ የተገለሉ ሰዎች እርዳታም ለመጠየቅ የማይደፍሩ ሰዎች ይኖሩታል። እኛ በተቻለን መጠን ወደነሱ በመሄድ ወይንም እርዳታ ለማግኘት ቀላል እንዲሆንላቸው በማድረግና በባህላቸውና ቋንቋቸው መሰረት የሚያናግሯቸው ሰዎችን በመጠቀም ተደራሽ ለመሆን እንጥራለን።
ድጋሚ ቢመረጡ ወንጀልን ለመቆጣጠር ምን ፕሮግራም አለዎት?
የወንጀል መበራከት ለካውንቲያችን ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ያለ ችግር ነው። ዋነኛው ምክንያቱ ደሞ ኮቪድን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ከስራ መቀነሳቸውና በዋናነት የተጠቁት ቀድሞውንም ዝቅተኛ ገቢ የነበራቸው ሰዎች መሆናቸው ዋነኞቹ ናቸው። ሬስቶራንቶችና ሱቆች እንደቀድሞው በሙሉ ኃይል አይሰሩም። ይህም ሰዎች ስራ አጥ እንዲሆኑና መተዳደሪያ እንዳይኖራቸው አድርጓል። እናም አንዳንድ ሰዎች ማድረግ በሌለባቸው ተግባራት ተሰማርተዋል። እናም ይህ ዋነኛው ችግር ነው። በተጨማሪም ኮቪድ የሰዎችን የአዕምሮ ጤና አዛብቷል። አንዳንድ ሰዎች ለ 2 አመት ያህል ከሌሎች ጋር አልተገናኙም። በተለይም በአስራዎቹ እድሜ ያሉ ታዳጊዎች ለ2 አመት ከሰው ሳይገናኙ መቆየታቸውና የተለመዱ ተግባሮችን ማከናወን ባለመቻላቸው ከአካባቢያቸው ማህበረሰብጋ መግባባትን አክብዶታል። ይህም አሁን ለሚታየው የወንጀል መበራከት አስተዋጾ አርጓል ብዬ አስባለሁ። ይህን ተከትሎ የአዕምሮ ጤና ተደራሽነትን በትምህርት ቤቶች አስፋፍተናል። ይህ ጥሩ ቢሆንም ችግር ያለባቸ ታዳጊዎች በአብዛኛው በትምህርት ቤት አለመገኘታቸው ችግር ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግ የማህበረሰብ ክሊኒኮች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ፕሮግራም ነድፌ ተግባራዊ አደርጋለሁ። በዚህም ፕሮግራም ወላጆች ወደሆስፒታል ሳይሄዱ ወይም በትምህርት ቤት ባሉ አገልግሎቶች ሳይገደቡ ልጆቻቸውን ይዘው መምጣት የሚችሉበት ወይም ራሳቸው ወላጆች እንዲገለገሉ እሰራለሁ። ከ20-30 አመት በፊት ካውንቲው የራሱ ክሊኒኮች ነበሩት አሁንም የሚያስፈልገን ያንን መመለስና ስደተኞችም ያለኢንሹራንስ መታከም እንዲችሉ ለማድረግ እንሰራለን። ሁሉም ነገር በትምህርት ቤቶች ብቻ መፍትሄ አያገኝም፤ ሁሉም ችግርም የአዕምሮ ደህንነት ችግር ብቻም አይደለም እንደውም በአብዛኛው የኢኮኖሚ ችግር ነው። የዝቅተኛ ደሞዝ መጠን መሻሻል አለበት። የዝቅተኛ የደሞዝ መጠን ወደ 15$ እንዲሻሻል 2 ጊዜ ተከራክሬያለሁ። ሆኖም አሁን ባለው ኢኮኖሚ 15$ ምንም ዋጋ የለውም። በሞንጎሞሪ ካውንቲ በዚህ ደሞዝ የሚከራይ ቤት ቢፈለግ አይገኝም። እናም የሰራተኞች ደሞዝ መሻሻል አለበት ሰራተኞች ጥቅማጥቅሞች ሊያገኙ ይገባል።
የሚወዱት የኢትዮጵያ ምግብ ወይም መጠጥ አለ?
መጠጥ ብዙም አይደለሁም። ከጠጣሁ ሻይ ወይንም ቡና ነው የምጠጣው። ጥብስ እወዳለሁ። የፆም በያይነት ላይ ምስርና አተርም ምርጫዬ ናቸው። እንጀራም በጣም እወዳለሁ። አሁን የስኳር ህመም ስላለበኝ እንደልብ ባልመገበውም ድሮ ግን 2-3 ቁርጥ እንጀራ እበላ ነበር። የአበላል ስታይሉንም እወደዋለሁ። በእጅ መመገብ የሚያዝናና ነገር ነው።
ከመጨረሳችን በፊት ለማህበረሰቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት ነገር አለ?
ለረጅም ጊዜ ከኢትዮጵያውያን ማህበረሰብጋ በቅርበት ስሰራ ቆይቻለሁ። አብዛኞቹ የተማሩና ቀርቦ ለመነጋገር ምቹ ናቸው። የተወሰኑት እንደመጡ የራሳቸውን ስራ ነው የጀመሩት። የሰው ልጅ እንዴት መተዳደር እንዳለበት የራሳቸው ግምትና አተያይ አላቸው። አድልዎና መገለል ሲያዩም ቀርበው ይናገራሉ። ችግራቸውንም ያስረዳሉ። እኔም በተቻለ መጠን ቀርቤ ለመስራትና ለማገዝ እሞክራለሁ። ለምሳሌ ቀጣይ ሳምንት የሚካሄደውን የእግር ኳስ ጨዋታ መተው ሲያናግሩኝ እምቢ አላልኩም። ከዩኒቨርሲቲውና ከ ፕሪንስ ጆርጅ ካውንቲ መንግስት ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን እንዲመቻችላቸው ረድቼያለሁ። ሞንጎምሪ ካውንቲን ያን ያህል አይጠቅመውም ግን ጨዋታዎቹን የታደሙ ሰዎች ማታ ማታ እዚህ መተው ማምሸታቸውና የኢትዮጵያውያንንና ሌሎች ምግብ ቤቶች ማዘውተራቸው አይቀርም። ሌላው ደሞ ካውንስሉ በቅርቡ ዘ-ቢድ የተሰኘ ህግ አፅድቆ ነበር። ከዚህጋ በተያያዘ በርካታ ኢትዮጵያአውያን ቅሬታ ያሰማሉ። ምክንያቱ ደሞ ካውንስሉ ያፀደቀው ህግ ራሱ ካውንስሉ ባሰራው ጥናት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ማይኖሪቲ የካውንቲው ነጋዴዎችን የሚጎዳ እንደሆነ እየታወቀ አሳልፈውታ። ይህ ህግ የካውንቲው ትልልቅ ባለኃብቶችና የቤት ባለንብረቶች የአነስተኛ ንግድ ባለቤቶችን ቀረጥ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ህግ ሲሆን እነዚህ አነስተኛ ነጋዴዎች ገንዘቡ የት እንደሚሄድና ምን እንደሚሰራበት ራሱ መወሰን አይችሉም። ከአማካሪነት የዘለለ ሚናም አይኖራቸውም። እንደኔ እንደኔ ይህ ህግ እንደ ኢትዮጵያውያን ሱቆችና ካፌዎች ካሉ አነስተኛው ነጋዴዎ ኃብትና ንብረታቸውን ቀምቶ ለካውንቲው ትልልቅ ባለኃብቶች እንደመስጠት እቆጥረዋለሁ። ይህ በፍጹም ትክክል አይደለም። ተቃውሜዋለሁ፤ ድምፅን በድምፅ በመሻር ስልጣንኔ ተጠቅሜ እንዳይጸድቅ አርጌያለሁ ብቸኛው የካውንስል አባል የተባበረኝ ዊል ጀዋንዶ ነው። መልካምነቱ የስቴቱ ህግ-አውጭ የህጉን ጎጂነት አይቶ እንዳይፀድ ወስኗል። ይህ ለእኔ በጣም ጠቃሚ ውሳኔ ነው። በፍፁም ባለሃብቶች ደኃውን ቀረጥ የሚያስከፍሉበት ስርዓት እንዲኖር አልፈቅድም።