የአለማችን ቁንጮ ባለኃብት ኢሎን መስክ ከመሰረታቸው አንዱ የሆነው ኒውራሊንክ የተባለው ድርጅት ላለፉት አመታት በእንስሳት አንጎል ላይ በተለይም በቺምፓንዚዎች አንጎል ላይ የማይክሮቺፕ ተከላ በማድረግ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን ይህ ማይክሮቺፕ (ጥንጥዬ ኮምፒውተር) የቺምፓንዚዎቹን የአዕምሮ የማሰላሰልና የማመዛዘን አቅም ያሻሻለ እንደሆነና ብዙ ውስብሰብ የሂሳብ ስራዎችን መስራት እንዳስቻላቸው ባለፈው ዓመት ኖቨምበር ወር ላይ አስታውቆ ነበር።
ይህ ኒውራሊንክ የተባለ ድርጅት ታዲያ ከሰሞኑ የአሜሪካ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በሰዎች ላይ ምርምሩን እንዲያደርግ ፈቃድ ሰጥቷል። ይህንንም በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
ምንም እንኳን ኒውራሊንክ በምርምር ወቅት እንስሳትን በማጎሳቆል ወንጀል በርካታ ክሶች ቢቀርቡበትም የሰው ልጅ ላይ ሙከራ እንዲያደርግ ከመንግስት ፍቃድ ከማግኘት አልገታውም።
ኢሎን መስክ ይህ ምርምር ከተሳካ በርካታ በሽታዎችን ለመፈወስ አይነተኛ አስተዋጾ ይኖረዋል ብሏል። ከነዚህም በሽታዎች በዋናነት ከአለመጠን መወፈርን፤ ኦቲዝምን፤ ድብርትና ድባቴን እና ስኪዞፍሬኒያ የተባለውን ከባድ የአዕምሮ ህመም ከማከሙም በላይ የተለያዩ ደረገጾችን በአዕምሮ ብቻ ለማየትና ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ይረዳል ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።
በዘርፉ ያሉ ተንታኞች ይህ ቴክኖሎጂ እውን ከሆነ የሰው ልጆች ልክ እንደስልክና ላፕቶፕ አንድ ተጨማሪ ቴክኖሎጂ በአዕምሯቸው እንደሚኖራቸውን ከተራ ዜጎች በተሻለ የመረጃ ተጠቃሚዎች የመሆን እድል እንደሚኖራቸው ጠቁመዋል። በተጨማሪም የሰዎችን ኃሳብና ድርጊት በመቆጣጠር ማህበረሰብን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራት ሊፈጸሙ እንደሚችሉ አክለው ተናግረዋል።