ባለፈው ሳምንት በሳውዝ ኢስት ዲሲ የማክዶናልድ ምግብ ቤት አቅራቢያ በፖሊስ ተተኩሶበት ለህልፈት የተዳረገውና በዲሲ ወንጀልን (ሁካታን) ለመቀነስ ይሰራ የነበረውን ጀስቲን ሮቢንሰን የተባለ ወጣትን ተኩሰው ሲገድሉ የሚያሳየው ቪዲዮ ትላንት በዲሲ ፖሊስ ለህዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡
ይህ ቪዲዮ መጀመሪያ እንዳይወጣ ሲባል ቆይቶ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን በአካባቢው ማህበረሰብና በቤተሰቦቹ ግፊት ምክንያት ይፋ ሊደረግ ችሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የዲሲ ከንቲባ ቢሮ የሟች ዘመዶችን የግለኝነት መብትና ደህንነት ለመጠበቅ ቪዲዮው እንደማይለቀቅ ተገልጾ የነበረ ሲሆን ይህም ዜጎች የመንግስትን ስራ በሚመለከት የወጣውንና መረጃዎችን ለህዝብ ክፍት እንዲሆኑ የሚያስገድደውን የአሜሪካንን ፍሪደም ኦፍ ኢንፎርሜሽን አክት የሚጻረር እንደነበር በርካቶች ሲተቹት ቆይተው ነበር፡፡
እሁድ 9/8 የሟች ቤተሰቦችና ጠበቃቸው ቪዲዮው እንዲለቀቅ በይፋ መጠየቃቸውን ተከትሎም የዲሲ ፖሊስ ቪዲኦውን ለህዝብ ይፋ አድርጎታል፡፡ ከቪዲዮው መለቀቅ በኋላም በርካቶች ቁጣቸውን ለመግለጽ በጎዳናዎች ወተው ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ እነዚህ ተቃውሞዎችም ወደኋላ ላይ ወደረብሻና ንብረት ጥፋት ተላልፈው እንደነበር እማኞች ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጲክ በጉዳዩ ያነጋገረቻቸው የሳውዝ ኢስት ዲሲ ነዋሪዎች ጀስቲን በፍጹም ይህ እንደማይገባው፤ የአካባቢው ታዳጊዎች ካላስፈላጊ ወንጀል እንዲርቁ በራሱ ተነሳሽነት ይሰራ እንደነበር ተናግረው የዲሲ ፖሊስ እርምጃ ተገቢ እንዳልሆነና ይልቅስ ከሳምንት በፊት የፖሊስ ባልደረባ በባረቀ ጥይት መሞቱን ተከትሎ የበቀል እርምጃ እንደሆነ እንደሚሰማቸው ተናግረዋል፡፡