ያለ ዕድሜ ጋብቻ በሰው ልጆች ላይ ከሚደርሱ የሰብዓዊ ጥሰቶች አንዱ ነው፡፡ በአለማችን በሚልየን የሚቆጠሩ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ያለፍላጎታቸው በወላጆቻቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው ተጽዕኖ እንዲያገቡ ይደረጋሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዩናይትድ ስቴትስ ከ2000 እስከ 2018 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ ከ10 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች ያለ ዕድሜያቸው ተድረዋል፡፡
ያለ ዕድሜ ጋብቻ ዋሽንግተን ዲሲን ጨምሮ በ37 ግዛቶች (ስቴቶች) ህጋዊ መሰረት አለው፡፡ ለምሳሌ በዋሽንግተን ዲሲ እድሜያቸው 16 ወይንም 17 የሆናቸው ታዳጊዎች ከወላጆቻቸው አንዱ ከተስማማ በማንኛውም ዕድሜ ካለ ሰውጋ በትዳር መጣመር ይችላሉ፡፡ ቨርጂንያ ያለ ዕድሜ ጋብቻን በ2020 ያስቀረች ሲሆን ሜሪላንድ በ2022 ባሳለፈችው ህግ የጋብቻ ዕድሜን ከ15 ወደ 17 ከፍ እንዲል ተደንግጓል፡፡ ከሰሞኑ ታዲያ የዲሲ ካውንስል አባላት በዲሲ ህጋዊ የጋብቻ ዕድሜን ወደ 18 ከፍ እንዲል የሚያስችል አዋጅ አርቅቀው አቅርበዋል፡፡ በ2023 በዋሽንግተን ዲሲ 15 ታዳጊዎች ተድረዋል ተብሏል፡፡
ያለ ዕድሜ ጋብቻ ሙሉ ለሙሉ የተከለከለው ከ50 የአሜሪካን ግዛቶች በ13ቱ ብቻ ነው፡፡