12/12/2024
Add a heading (3)

ካሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ኦክቶበር 1 2024 ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው አዲሱ የዲሲ ህግ መሰረት የዲሲ መንግስት በተደጋጋሚ ጥፋት ያጠፉ የሜሪላንድና የቨርጂንያ አሽከርካሪዎችን መክሰስ የሚችልበት ህግ ተግባራዊ ሆኗል። ይህ ስቲር አክት የተባለው ህግ (Strengthening Traffic Enforcement, Education and Responsiblity Amendment Act of 2024 (STEER Act)) በዋናነት በ6ኛው ወረዳ የካውንስል አባል በሆኑት በቻርልስ አለን የቀረበ ረቂቅ ህግ ነበር።

ዲሲ እስካሁን ድረስ ከዲሲ ውጭ ያሉ አሽከርካሪዎችን ምንም ያህል የትራፊክ ቅጣት ቢኖርባቸው መጠየቅ የሚያችል ህግ አልነበራትም። በዚህም ምክንያት የሜሪላንድና የቨርጂንያ አሽከርካሪዎችን ጨምሮ በ2022 ብቻ ከ 880 ሚልየን ዶላር በላይ ያልተከፈለ የትራፊክ ቅጣት እንዳለ ታውቋል።

የWUSA ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ ከኦክቶበር 2020 እስከ ማርች 2021 ባለው ጊዜ ከተሰጡና ካልተከፈሉ የትራፊክ ካሜራ ቅጣቶች 75% የሚሆኑት የሜሪላንድ አሽከርካሪዎች ያገኙት ትኬት ነው።

በአዲሱ የስቲር አክት ህግ መሰረት በአደገኛ ሁኔታ የሚያሽከረክሩ የሜሪላንድና ቨርጂንያ አሽከርካሪዎች በፍርድ ቤት ተከሰው ወንጀለኛ ከተባሉ ከትኬት ቅጣት በተጨማሪ መኪናቸው ላይ በሚገጠም ማሽን የመኪናቸው ፍጥነት ከመንገዱ የፍጥነት ወሰን በላይ እንዳይሄድ እንደሚደረግ ተነግሯል።

በተጨማሪም በአዲሱ ህግ መሰረት አሽከርካሪዎች በመኪናው ላይ ነጥቦች የሚያዝባቸው ሲሆን በ6 ወር ውስጥበፍጥነት በማሽከርከር ወይም ሌላ የትራፊክ ቅጣቶች በተደጋጋሚ ካደረሱ መኪናቸው እንደሚወረስ/ቶው እንደሚደረግ ተነግሯል።

በዚህ አዲስ ህግ መሰረት ከተመደበው ፍጥነት ከ11 እስከ 15 በላይ ሲያሽከረክሩ የተያዙ ሁለት ነጥብ ከ16-19 ማይል በላይ ሲያሽከረክሩ የተያዙ 3 ነጥብ 20 ማይልና ከዛ በላይ ሲያሽከረክሩ የተያዙ 5 ነጥብ የሚያገኙ ሲሆን ሞገደኛ አሽከርካሪዎች ደሞ እስከ 10 ነጥብ ሊያገኙ ይችላሉ ተብሏል።
በ6 ወር ውስጥ 10ና ከዛ በላይ ነጥብ ያገኙ መኪኖች እንዳይንቀሳቀሱ ጎማ ማሰሪያ ይገጠምባቸዋል ወይም ቶው ይደረጋሉ። ይህ የነጥብ ስርዓት አሁን በስራ ላይ ካለውና መንጃ ፍቃድ ላይ ከሚደረገው የነጥብ ስርዓት የተለየ ሲሆን የመንጃ ፍቃድ ነጥብ በህግ አስከባሪዎች (በፖሊስ ተይዘው ሲቀጡ) ብቻ የሚሰጥ እንደሆነ የመኪና ነጥብ ግን በፍጥነት ካሜራና በመብራት ካሜራዎችም እንደሚሰጥ ተነግሯል።
በተጨማሪም በአዲሱ ህግ የተሰረቁ መኪናዎች የሚያገኟቸው ትኬቶችን የመኪናው ባለቤት ከመክፈል ነጻ እንዲሆን ይደነግጋል። ከዚህ ቀደም ይህ ህግ ባለመኖሩ መኪናቸው የተሰረቀባቸውን ሰዎች ዲኤም ቪ ካልከፈላችሁ ብሎ ያስጨንቅ እንደነበርና አዲሱ ህግ ግን ይህን የተጎጆችን ጭንቀት እንደሚያስቀር ተነግሯል።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት