
በ2025 በኮንግረስ የጸደቀውና ማንኛውም በአሜሪካ የሚኖር ሰውን ማንነት በአግባቡ ይገልጻል የተባለለት የሪል አይዲ ህግ ከመጪው ሜይ 7 ጀምሮ ወደተግባር ይገባል። ይህ ህግ ስቴቶች በመታወቂያና መንጃፍቃድ ላይ ከወትሮው በተለየ ጠበቅ ያለ ቁጥጥርና መታወቂያ ወይንም መንጃ ፍቃድ ከመስጠታቸው በፊት የሚያስፈልጉ ማስረጃዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንዲኖር ያደርጋል።
ከሜይ 7 በኋላም ይህ አይነት መታወቂያ ወይንም መንጃ ፍቃድ የሌላቸው ሰዎች በአገር ውስጥ በረራ ለማድረግ ወይንም የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ለመግባት እንደፓስፖርት ያለ ሌላ ተጨማሪ የመታወቂያ ወረቀት ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
ይህ ህግ በዋናነት ከ9/11 የኒው ዮርክ ጥቃት በኋላ የፌደራል መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር እንዲኖር ባወጀው መሰረት እንዲተገበር የታለመ ህግ ሲሆን ህግ ሆኖ ከጸደቀበት ጊዜ አንስቶ እስካሁ ድረስ በተለያዩ ጉዳዮች ተፈጻሚ ሳይሆን ሲንከባለል ቆይቶ ነበር።
ይህን የሪል አይ ዲ (መታወቂያ) ለማግኘት ነዋሪዎች ምን ያስፈልጋቸዋል?
ይህንን መታወቂያ/መንጃ ፍቃድ ለማግኘት ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የዲኤምቪ ቢሮ በመሄድ ማንነታቸውን የሚገልጽ ሌላ ወረቀት (እንደ ቀኑ ያላለፈ ፓስፖርት፤ ወይንም የልደት ሰርተፊኬት)፤ የሶሻል ሴኩሪቲ ካርድ፤ ለሚኖሩበት ቤት ኗሪነታቸውን የሚያረጋግጥ ወረቀት (የሊዝ ወረቀት፤ የዩቲሊቲ ቢል የመሳሰሉ)፤ እና በአሜሪካ በህጋዊነት የመገኘት ፍቃድ(Lawful U.S Presence) (ከግሪን ካርድ ይለያል) (በጊዜያዊም ቢሆን) የሚያሳዩ መረጃዎችን በመያዝ ይህን አዲስ መታወቂያ ማግኘት ይቻላል።

አሁን ያለዎት መታወቂያ ወይንም መንጃ ፍቃድ ሪል አይዲ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዴት ይታወቃል?
የሪል አይዲ መታወቂያ በዋናነት ከድሮው መታወቂያ/መንጃፍቃድ የሚለየው በላዩ ላይ የወርቃማ ወይንም ጥቁር የኮከብ ምልክት ይኖረዋል። መታወቂያዎ ወይንም መንጃፍቃድዎ ይህ ኮከብ ከሌለው ሪል አይዲ አይደለም።
ሪል አይዲ ባይኖርዎት ምን ይፈጠራል?
አይ አልፈልግም በድሮው መታወቂያዬ/መንጃፍቃዴ እቀጥላለው ካሉ መብትዎ ነው። በዚህ አሮጌ መታወቂያ መኪናዎን መንዳት፤ ምርጫ ላይ መሳተፍ ወይን ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ። በዋናነት በአገር ውስጥ በረራ ለማድረግ ከፈለጉ ወይንም የፌደራል መስሪያቤቶች ውስጥ ጉዳይ ኖሮት ለመግባት ከፈለጉ ያለሪል አይዲ ሌላ እንደፓስፖርት ያለ መታወቂያ ማቅረብ ግድ ይሎታል።
ለበለጠ መረጃ የዲሲ ዲ ኤም ቪ ስለ ሪል አይዲ የሚያትትበትን ገጽ ይህን ሊንክ ተጭነው ይመልከቱ።