
ፕሬዘደንት ትራምፕ ማርች 14 ማምሻውን በፈረሙት ኤክስኪውቲቭ ኦርደር የቪኦኤ የበላይ የሆነውን የዩናይትድ ስቴትስ ኤጀንሲ ፎር ግሎባል ሚዲያን ህጉ በሚፈቅደው መጠን የሰራተኛና የወጭ ቅነሳ እንዲያደርግ ማዘዛቸውን ተከትሎ ከማርች 15 ጀምሮ ሁሉም ሰራተኞች ላልተወሰነ ጊዜ አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ የሚያዝ ኢሜይል ደርሷቸው ነበር::
በዚህ ውሳኔ መሰረትም የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ከአየር ላይ ጠፍቶ የቆ የ ሲሆን ሰራተኞችና ሌሎች የሚዲያ ጣቢያው ተቆርቋሪዎች የፌደራል መንግስትን ከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ከርሟል።
ዛሬ ይህንኑ ጉዳይ ለመስማትና ብይን ለመስጠት ተቀምጠው የነበሩት የፌደራል ፍርድ ቤት ዳኛ ሮይስ ላምበርዝ ታዲያ በፕሬዘደንት ትራምፕ የተሾሙት የዩ ኤስ ጂ ኤም ፕሬዘደንት ቪ ኦ ኤና ሌሎቹን በስሩ ያሉ የሚድያ ተቋማትን ሲዘጉ ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ እንደዘጉና በህገወጥ መንገድ የተወሰነ ውሳኔ ነው በማለት አግደውታል።
ዳኛው አክለውም የዩ ኤስ ኮንግረስ እነዚህ ተቋማት በጀት መድቦ እውነተኛና ሀቀኛ ዜናዎችንና መረጃዎችን ለቀሪው አለም እንዲያደርሱ የተቋቋሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔ ቪ ኦ ኤ፤ ራዲዮ ፍሪ ኤዥያ፤ና የሚድል ኢስተርን ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክን ለአሁኑ ከመፍረስ ይታደጋል ተብሏል።
በዚህ ውሳኔ መሰረትም የትራምፕ አስተዳደር በአስተዳደራዊ እረፍት ላይ ያስቀመጣቸውን ከ1000 በላይ ሰራተኞች ወደ ቀድሞ ስራቸው እንዲመልስና ስርጭት እንዲጀምር ታዟል።