
ዲጄ ሲምባ በመባል የሚታወቀው ወጣት ዳዊት ክንፈ ሳህሉ ገበታ ላይ ቀርቦ በድንገት ህይወቱ ካለፈ ትላንት አንድ ሳምንት ሞላው።
የአንዲት ሴት ልጅ አባት ከሆነ የሁለት ሳምንቱ ብቻ የነበረው ወጣቱ አባት ባልታሰበ እና ምንነቱ ባልታወቀ ሁኔታ ምግብ ለመመገብ ገበታ ላይ ቀርቦ ሳለ ህይወቱ ማለፉን ወዳጆቹ ይናገራሉ።
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከመጣ ስድስት ዓመታት አካባቢ እንደሆነው እና ከአንድ አመት በፊት ወደ አትላንታ በማቅናት፤ ትዳር መስርቶ መኖር መጀመሩን ባለንጀሮቹ ተናግረዋል።
በአትላንታ በተለያዩ ቦታዎች በተለይም ‘ላየንስ’ በተባለ ስፍራ በዲጄነት ይሰራ እንደነበር አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም በተለየ ሁኔታ የሚታወቅ ምንም ዓይነት በሽታ እንደሌለበት የሚናገሩት ጏደኞቹ እስካሁን ድረስ ፖሊስ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እንዳላስታወቀ ጠቁመዋል። የፖሊስ ምርመራ ሲጠናቀቅ አስክሬኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላክ እና ቀብሩ በዛ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
የቅርብ ጓደኞቹ ቤተሰቦቹን በተለይም የዲጄ ሲምባ አዲሲቷን ጨቅላ ህጻን ቅርስ ኖሯት እንድታድግ ለመርዳት የሚያግዝ ነው ያሉትን የጎፈንድ ሚ ድጋፍ በመክፈት እርዳታ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ::