
የበርካቶች ምርጫ የሆነውና በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ፀሀይ የኢትዮጵያ ባርና ሬስቶራንት ለ2025 የአመቱ ዘና ፈታ ያለ ሬስቶራንት በሚል ዘርፍ (Casual Restaurant of the Year) ለሽልማት ታጭቷል።
ዘ ራሚስ የሽልማት ፕሮግራም በሬስቶራንት አሶሴሽን ኦፍ ሜትሮፖሊታን ዋሽንግተን (Restaurant Association Metropolitan Washington (RAMW)) የሚዘጋጅና በአካባቢያችን ያሉ ምርጥ የተባሉ አገልግሎት ሰጪዎች የሚወደሱበት የዕውቅና መስጫ ፕሮግራም ነው።
በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ላይ ያሉ ዳኞች በምስጢራዊ መንገድ ድምጻቸውን የሚሰጡ ሲሆን ከመጀመሪያው ዙር ቀጥሎ የህዝብ ምርጫ መሰብሰቢያ ከሜይ 1 እስከ ሜይ 31 እንደሚኖርም ተነግሯል።
ይህ የህዝብ ምርጫ መሰብሰቢያ በኤን ቢ ሲ ዋሽንግተንና በቴሌሙንዶ ድረገጾች የሚከናወን ይሆናል።
የዚህ ውድድር የመጨረሻ አሸናፊዎች ማንነትም በኦገስት 3 2025 በዋልተር ኢ ዋሽንግተን ኮንቬንሽን ሴንተር በሚደረገው የሽልማት ስነስርዓት ይፋ ይሆናል።

ፀሀይ ሬስቶራንት ጆርጂያ አቬኑ ላይ ሻው አካባቢ ከነበሩበት ተነስተው በ2023 በአዳምስ ሞርጋን አካባቢ የከፈቱ ሲሆን የሬስቶራንቱ ባለቤት ሰላም መኩሪያ ምግብ ቤቱን በእናቷ ስም እንደሰየመችውና አብዛኛውን ሙያም ከእናቷ እንደቀሰመች በምግብ ቤቱ ድረገጽ ላይ ተቀምጧል።
የሰላም እናት ወይዘሮ ፀሀይ ትውልዳቸው በሀረርጌ ሲሆን ኋላም ወደ አዲስ አበባ እንደመጡና ልጆቻቸውን ለመደገፍ የምግብ ቤት እንደከፈቱ ያም በርካታ ደንበኞች እንዲያፈሩ እንደረዳቸውና በሙያቸውም የተወደዱ እንደነበሩ እዚሁ ድረገጽ ላይ ተጠቅሷል። ሰላምም ከእናቷ ስር በመሆን ሙያቸውን እንደቀሰመችና ልክ እንደ እናቷ አሁንም ድረስ አብዛኛውን ግብዓት በባህላዊ መንገድ እናዘጋጃለን ብለዋል።
ፀሀይ ሬስቶራንት እጩ በሆነበትና የአመቱ ዘና ፈታ ያለ ሬስቶራንት በሚል ዘርፍ (Casual Restaurant of the Year) በተባለው ዘርፍ የታጩት ሌሎች ሬስቶራቶች 2ፊፍቲ ቴክሳስ ባርቢኪው(2Fifty Texas BBQ)፤ ዘ ፎልስ(The Falls)፤ አይ ኤግ ዩ(I Egg You)ና ስቴሊና ፒዜሪያ (Stellina Pizzeria) ይገኙበታል።
የራሚ ሽልማት እጩዎችን ለማየት ይህን ይጫኑ