
By SASHA ALLEN, AUDREY KEEFE and ADAM HUDACEK – Capital News Service –
Translated & Modified by Ethiopique Staff
የሜሪላንድ ባልቲሞር የካቶሊክ በጎ አድራጎቶች ድርጅት የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ተገቢ የሆነ የድጋፍ አገልግሎቶችእንዲያገኙ ለማድረግ፤ እና በሦስት የሜሪላንድ የሕዝብ ትምህርት ቤት ዲስትሪክቶች ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ ከትምህርት ቤት የመቅረት ችግርን ለመቅረፍ፤ ከግዛቱ የገንዘብ ድጋፍ ድጎማዎችን አሸንፈዋል።
ትራይቭ ቢሄቪየራል ሄልዝ የተሰኘው ተቋም በአምስት የት/ቤት ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ የስነምግባር ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይቀሩ እና እንዲታረቁ ለማድረግ የገንዘብ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፤ መርሃግብሩ ውጤታማ እንደነበር ገልጿል።
የዓለም የጤና ድርጅት በአለም ዙሪያ እድሜያቸው ከ10-19 ከሆኑ ሰባት ታዳጊዎች መካከል አንዱ በአዕምሮ ጤና እክል እንደሚያጋጥማቸው አስታውቋል። ወጣቶችን ከሚያጋጥሟቸው የአዕምሮ ጤና ችግሮች መካከል ድባቴ፣ ጭንቀት፣ የባህሪ ችግሮች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
ታዳጊ ልጆች በሰውነታቸው ውስጥ በሚፈጠር የሆርሞን መዛባት፣ በቂ እንቅልፍ ማጣት፣ ከአቻ ግፊት ጋር ተያይዞ በሚመጡ ጫናዎች፣ የሚኖሩበት አካባቢ የሚያስከትለው ጫና ከልክ በላይ በሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በድህነት እና በመሳሰሉት የተነሳ ለአዕምሮ ህመም እንደሚጋለጡ ጥናቶች ያመላክታሉ።
በተለይም ከስደተኛ ቤተሰብ የተወለዱ ልጆች ከሌሎች አቻዎቻቸው በላቀ መልኩ ለአዕምሮ ጤና እክል የተጋለጡ ናቸው።
በአጠቃላይ፣ እነዚያን ሁለት ጥረቶች የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው አዲሱ የክልል የወጣቶች የአዕምሮ ጤና ድጋፍ መርሃግብር፤ እ.ኤ.አ ከመጋቢት እስከ ጥር 2024 ባሉት የመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ውስጥ ከ58,000 ለሚበልጡ ተማሪዎች የባህሪ ጤና አገልግሎትን ድጋፍ አድርጓል። ጥናቶች ሜሪላንድ ውስጥ ካሉ ከአምስት የህዝብ ትምህርት ቤቶች አራቱ በግዛቱ የሚደገፍ ተነሳሽነት አማካኝነት የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ድጋፍ አላቸው።
ይሁን እንጂ አጠቃላይ ጉባኤው የሜሪላንድን የ2025 የበጀት ዓመት፤ ከባለፈው ዓመት ጸደይ ውቅት ጋር ለማመጣጠን በተንቀሳቀሰበት ወቅት፣፤ የግዛቱ ህግ አውጪዎች ለታዳጊ ወጣቶች የአዕምሮ ጤና ፕሮግራም በሀገረ ገዥው ዌስ ሙር ማካኝነት ከ110 ሚሊዮን ዶላር እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ለመቀነስ መክረዋል። እና የግዛቱ የበጀት ችግሮች እየሰፉ በመጡበት ወቅት፣ ሀገረ ገዥው ዌስ ሙር በአንድ ወቅት 130 ሚሊዮን ዶላር ሊሰጠው ይገባል ለው የነበረውን መርሃግብር ሃሳባችውን በመቀየር እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ በየዓመቱ እንዲምደብለት ጠይቀዋል። ሀገረግዥው ለዚህ ሃሳባቸው በምክንያትነንት ያነሱት ሜሪላንድ ግዛት የሦስት ቢልየን ዶላር የበጀት ክፍተት ስላለባት መሆኑን አስታውቀዋል።
በትራይቭ የባህርይ ጤና የማኅበራዊ ጉዳዮች ባለሞያዋ ሜጋን ፓንቴሊስ፤ የበጀት ቅነሳቅ በግዛቱ ያሉ እጅግ ብዙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ታዳጊዎችን እንደሚጎዳ አስታውቀዋል።
ጠቅላላ ጉባኤው እ.ኤ.አ 2022-23 የትምህርት ዘመን የሜሪላንድ የጤና ክፍል ባድረገው የዳሰሳ ጥናት፤ ከሩብ በላይ የሚሆኑ የሜሪላንድ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የአዕምሮ ጤንነታቸው ከሞላ ጎደል መልካም እንዳልሆነ ማስታወቃቸውን ተከትሎ በጀቱ እንዲመደብ ወስኖ ነበር።
መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ሚድል ስኩል) ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አንጻር የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው ታዳጊዎች አሃዝ ዝቅተኛ ቢሆንም 22 ከመቶ የሚሆኑት የአዕምሮ ጤንነታቸው ቢበዛም ሆነ ሁልጊዜ ጥሩ እንዳልሆነ፣ የሀዘን እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳላቸው ተናግረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ተቋም CDC በአሜሪካ 40 ከመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ተማሪዎች የተስፋ መቁረጥ እና የድብርት ስሜት እንዳለባቸው በመግለጽ ትምህርትቤቶች እና ግብረሰናይ ተቋማት በዚህ ዙሪያ እንዲሰሩ መክሯል።
ከበጀት ጋር ተያይዞ ባሉ ክርክሮች እና ውይይቶችም በቅርቡ ውሳኔ ያገኛሉ።
ለመሆኑ ከታዳጊ ልጆች የአዕምሮ ጤናጋር ተያይዞ ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድናቸው?
የስሜት መቃወስ
በጉርምስና ዕድሜ ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ የስሜት መቃወስ የተለመደ እና የሚያጋጥም መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት መረጃዎች ያመላክታሉ። የጭንቀት መታወክ ድንጋጤን አሊያም ከመጠን ያለፈ ጭንቀትን ሊያጠቃልል ይችላል። ይህ ሁኔታ በተለይም በዚህ ወደ ጉርምስና እየገቡ ባሉ ወንዶች ላይ በብዛት ያጋጥማል።
የጭንቀት እና የድባቴ ስሜቶች በታዳጊዎች የትምህርት ፍላጎት እና ውጤታማነት ላይ በትምህርት ቤት ስራ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ። በተጨማሪም ማኅበራዊ መገለልን እና ብቸኝነትን ያመጣሉ። ሁኔታው በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለትም የመንፈስ ጭንቀት እና ራስን ማጥፋት ሊያስከትል ይችላል።
የባህሪ መቃወስ
የባህሪ መቃወስ በተለይም በለጋ ታዳጊዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን በተለይም የትኩረት ማጣት እና ከልክ በላይ መቅበጥብጥ (ADHD) ይታይባቸዋል። ይህ ሁኔት በወላጆች፣ በመምህራን እና ብሎም በሀኪሞች በጊዜ ካልታገዘ የትምህርት ውጤት ማሽቆቆል እና በኋላም ወደ ወንጀል በሚያመሩ ሁኔታዎች ውስጥ የመሳተፍ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል።
የአመጋገብ መቃወስ
የአመጋገብ ቀውስ አብዛኛውን ጊዜ ከተክለ ቁመና እና የሰውነት ቅርጽ ጋር ተያይዘው በሚመጡ የስሜት መለዋወጦች ጋር ይያያዛል። አብዛኛውን ጊዜም ከወንዶች ይልቅ እድሜያቸው ከ14-19 ባሉ በልጃገረድ ታዳጊዎች ላይ ይታያል። ምግብ መመገብ መቀነስ፣ የበሉትን ምግብ መልሶ ማስወጣት፤ አሊያም በጭንቀት የተነሳ አለቅጥ መመገብ የችግሩ መገለጫዎች ናቸው።
ከልክ በላይ አደጋ መዳፈር
በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርስ እንደ ሱስ መጠቀም፣ ለአደጋ የሚያጋልጡ ጌሞች እና ጨዋታዎች እንዲሁም የጾታ ግንኙነቶችን መዳፈር የመሳሰሉት በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። በዚህ እድሜ የሚጀመር ሱስ እና አንዳንድ ተሞክሮ በዘላቂነት ሊቀጥል እንደሚችል ባለሞያዎች ይናገራሉ።

መፍትሄዎች
ስደተኛ ወላጆች ባህል ለልጆቻቸው ለማስተማር በእጅጉ የሚጥሩ ሲሆን፤ ይሁን እንጂ የሀገሪቱን ባህል ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት፣ ወቅታዊ የሆኑ የልጆቻቸውን የባህሪ ለውጦት በቅርበት መከታተል፣ ከመቆጣት ይልቅም የችግሩ መንስኤ አስቀድሞ በመረዳት ከልጆቻቸው ጋር መፍትሄ መፈልግ ላይ እንዲያተኩሩ ባለሞያዎች ይመክራሉ።
በተጨማሪም በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ከአዕምሮ ጤና እና ከሱስ ጋር ተያይዘው የሚሰሩ ተቋማት ድጋፍ መጠየቅ ይመከራል። በተጨማሪም ታዳጊዎቹ በሚማሩባቸው ት/ቤቶች ውስጥ የድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ መምህራን እና መረጃዎች ያሉ ሲሆን የቋንቋ ድጋፍ ለማግኘት መጠየቅ ይቻላል።
ለታዳጊ ልጆች የአዕምሮ ጤና ዙሪያ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት ከታች ተዘርዝረዋል።
ዲሲ፦ community based mental health providers
ሜሪላንድ፦ https://211md.org/resources/mental-health/teen-support/
ቨርጂኒያ፡ – https://nami-northernvirginia.org/

አማርኛ ተናጋሪ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት
በቅርቡ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተፈረመው እንግሊዘኛ የሀገር ቋንቋ እንዲሆን የሚያዘው ልዩ ህግ ምናልባት በአማርኛ፣ ትግረኛ እና አፋን ኦሮሞ ለወላጆች እና ለልጆች ይሰጡ የነብሩ የትርጉም ድጋፎችን ሊያስቀር የሚችል በመሆኑ በአማርኛ ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማትን ከታች ዘርዝረናል።