@ethiopique202 (64)

ሜይ 12 ቀን 2025 የተወካዮች ምክር ቤት ሪፐብሊካኖች (House Republicans) የፌደራል የሜዲኬይድ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ አዲስ የበጀት እቅድ አስተዋውቀዋል። የመንግስት ወጪን ለመቀነስ እና የ4.5 ትሪሊዮን ዶላር የታክስ ቅነሳን ለማራዘም ለሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል የሆነው ይህ ሀሳብ በሚቀጥሉት አስር አመታት ወደ 880 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከሜዲኬይድ እንዲቀነስ ይጠይቃል።


ከእቅዱ ዋና ዋና ድንጋጌዎች መካከል አንዱ በስራቸው የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ወይንም ጥገኞች የሌላቸውን አዋቂዎች ላይ አዲስ የሥራ መስፈርቶችን ያካትታሉ፤ ይህም ሽፋናቸውን ለመጠበቅ ና ኢንሹራንሳቸው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል እኚህ ሰዎች በወር ቢያንስ 80 ሰዓታት ስራ መስራት ወይም የበጎ ፍቃድ ማህበረሰብ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ሁኔታ የማህበረሰብ ተሳትፎ ማለት አንድ ሰው በወር ቢያንስ ለ80 ሰዓታት እየሰራ መሆኑን፣ ትምህርት ቤት ወይም የሥራ ስልጠና እየተከታተለ መሆኑን፣ በበጎ ፈቃደኝነት እየሰራ መሆኑን ወይም የተፈቀደ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ማሳየት አለበት ማለት ነው።

እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት ካልቻሉ ወይም በአግባቡ ሪፖርት ካላደረጉ የሜዲኬይድ ሽፋናቸውን ሊያጡ ይችላሉ። ተቺዎች ይህ በተለይ ያልተረጋጋ ስራ ላላቸው፣ የቋንቋ ችግር ላለባቸው፣ የልጆች ወይም የሌሎች ሰዎችን እንክብካቤ ኃላፊነት ላለባቸው ወይም የትራንስፖርት አገልግሎት ለማግኘት ለሚቸገሩ ሰዎች ተጨማሪ ሸክም ሊፈጥር እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።
ይህ ዛሬ የቀረበው ረቂቅ በተጨማሪም የሜዲኬይድ ተጠቃሚዎች የገቢ ማረጋገጫ ሂደቶችን በማጠናከር ግለሰቦች በዓመት ሁለት ጊዜ የፋይናንስ ብቁነታቸውን እንዲያድሱ ይጠይቃል። በተጨማሪም ስቴቶች የሜዲኬይድ ፕሮግራሞቻቸውን በአቅራቢዎች ታክስ እንዴት እንደሚደግፉ ያሉ ሂደቶች ላይ ለውጦችን እንዲኖሩ የሚተይቅ ሲሆን፤ ይህም የጤና ባለሞያዎችና ተያያዥ አገልግሎት ሰጪዎች ክፍያቸውን የሚያገኙበትን መንገድ ሊቀይር ይችላል ተብሏል።
የዴሞክራት ህግ አውጪዎች ወዲያውኑ ማስጠንቀቂያ የሰጡ ሲሆን ይህ እቅድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የጤና ሽፋን ሊያሳጣ እና በአፎርደብል ኬር አክት ስር የጤና ኢንሹራንስ ያላቸውን ሰዎች ሊጎዳ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ከኮንግረሽናል በጀት ጽህፈት ቤት የወጣው የመጀመሪያ ግምት ይህ ሀሳብ ህግ ተግባራዊ ቢደረግ እስከ 8.6 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በአስር አመታት ውስጥ ሽፋን ሊያጡ እንደሚችሉ ይጠቁማል። የህግ አውጪዎች እና የድጋፍ ቡድኖች እነዚህ ቅነሳዎች የሆስፒታሎች መዘጋት፣ ለአረጋውያን የሚሰጡ አገልግሎቶች መቀነስ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች ከፍተኛ የኪስ ወጪ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

በምላሹ በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ አካባቢ ያሉ የማህበረሰብ ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የጤና ተሟጋቾች፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ ክሊኒኮች እና ስደተኞችን የሚያገለግሉ ቡድኖች ነዋሪዎች ሊኖሩ የሚችሉትን ለውጦች እና የጤና አገልግሎታቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ እንዲረዱ የመረጃ ስብሰባዎችን እና የማስተማር ዘመቻዎችን እያዘጋጁ ነው። አንዳንዶች ከአካባቢው ተወካዮች ጋር ስብሰባዎችን እያቀዱ ሲሆን ማንኛውም የመጨረሻ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ነዋሪዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እያበረታቱ ነው።


በተቃራኒው ይህንን ረቂቅ ህግ የሚደግፉ ሰዎችና ተቋማት ይህ ረቂቅ የታክስ ከፋዩን ህዝብ ገንዘብ በአግባቡና ሀላፊት በሚሰማው መልኩ እንዲወጣ እንደሚያደረግና አላስፈላጊ ወጪዎችን እንደሚያስቀር እንደሚያምኑ ተናግረዋል። አልፎ ተርፎም ለሰራተኛ ቤተሰቦች የታቀደውን የግብር ቅነሳ ተግባራዊ ለማድረግ ይህ አካኄድ አይነተኛ አስተዋጾ ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.