@ethiopique202 (63)

ግንቦት 9፣ 2025፣ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ስቴፈን ሚለር አስተዳደሩ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከሀገር በፍጥነት ለማስወጣት በህገመንግስቱ የተደነገገውንና መሰረታዊውን የሪት ኦፍ ሀቢየስ ኮርፐስን መብት ለማገድ እያሰበ መሆኑን ተናግረዋል።


ሀቢየስ ኮርፐስ ምንድን ነው?
ሀቢያስ ኮርፐስ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሰዎች በፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸውን እንዲያስረዱና የታሰሩበት ጉዳይ አግባብ እንዳልሆነ ማስረዳት የሚችሉበት የህግ ጥበቃ ነው። መንግስት አንድን ሰው ዳኛ ፊት ቀርቦ ጉዳዩን እንዲያስረዳ እድል ሳይሰጠው መያዝና አስሮ ማቆየትን ይከላከላል። ይህ ጥበቃ በአሜሪካ ህግ ውስጥ ካሉት በጣም አስፈላጊ ጥበቃዎች አንዱ ነው።

አሁን ምን ተፈጥሮ ነው ይህ ህግ ይነሳ የተባለው?
የትራምፕ አስተዳደር በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ድንበር ሾልከው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ “ወረራ” እንደተፈጸመ ይናገራል። የመንግስት አማካሪው ስቴፈን ሚለር ታዲያ እንዲህ ባለ የአገር ወረራ ወቅት ሀቢየስ ኮርፐስን ማስቆምና ሰዎችን ያለ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብነት ከአገር ማስወጣት እንደሚቻልና ህገ መንግስቱ ሀቢያስ ኮርፐስን “በዓመፅ ወይም በወረራ” ጊዜ ብቻ እንዲታገድ ስለሚፈቅድ ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ተደምጠዋ። ይህ ወሳኝ የህግ ከለላ ከታገደ መንግስት በርካታ ስደተኞችን ጉዳያቸውን በአግባቡ ሳያይና በፍርድ ቤት ቀርበው የማስረዳት ዕድል ሳይሰጥ ሰዎችን ማባረር ይችላል።


ይህን ማድረግ ህጋዊ ነውን?
ባለሙያዎች ይህ እርምጃ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እና ህገ-መንግስታዊ ያልሆነ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። በተጨማሪም ሀቢየስ ኮርፐስን ማገድ የሚችሉት ፕሬዚዳንቱ ሳይሆኑ ኮንግረስ ብቻ ነው— ኮንግረስም ቢሆን ለማገድ አገሪቱ እጅግ ከባድ ሁኔታ ውስጥ መግባት ይኖርባታል። ይህን አይነት እርምጃ ከዚህ ቀደም እጅግ አልፎ አልፎ እንደ በአሜሪካ የእርስበርስ ጦርነት ወቅት፤ በሁለተኛው የአለም ጦርነትና በመሳሰሉ ጊዜያት ነበር ተግባራዊ የሆነው።


ሀቢየስ ኮርፐስ ከታገደ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በህጋዊ ሂደት ላይ እያሉ ጉዳያቸው በኢሚግሬሽን ቢሮ ሳይታይላቸው ወይንም የኢሚግሬሽን ዳኛጋ ሳይሄዱ በፊት ከአገር ሊባረሩ ይችላሉ። የስደተኞች መብት ተሟጋች ቡድኖች እና የህግ ምሁራን ይህ የሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ እና የአሜሪካን የህግ ስርዓት ዋና ዋና ክፍሎችን የሚያዳክም ነው በማለት ከፍተኛ ስጋት አላቸው።

ቀጣዩ ምንድን ነው?
የትራምፕ አስተዳደር ይህንን እርምጃ በይፋ አልወሰደም፣ ነገር ግን የስቴፈን ሚለር መግለጫ በቁም ነገር እየታሰበበት መሆኑን ያሳያል። በርካቶች ታዲያ ይህ አካሄድ የአሜሪካ ዜጎችንም አደጋ ውስጥ ሊከት እንደሚችል ፍራቻቸውን ያስቀምጣሉ። የስደተኞች መብት ተከራካሪዎችና የህግ አውጪዎች ከአሁኑ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ይህ ውሳኔ ተግባራዊ ከሆነም በህጋዊ መንገድ እንደሚታገሉት አስታውቀዋል።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.