
የትራምፕ አስተዳደር ህገ ወጥ ያላቸውንና ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ አገር አሻግሮ ለመላክ ሩዋንዳን ጨምሮ ከበርካታ አገራትጋ እየተደራደረ እንደሆነ ይታወቃል።
ከሰሞኑ ታዲያ ሾልከው ወጡ የተባሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የትራምፕ አስተዳደር ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ ስደተኞችን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የባርያ ንግድ በተስፋፋባት በተለይም ለስደተኞች ሲዖል እንደሆነች ወደሚነገርላት ሊቢያ ዲፖርት ሊያደርግ እንደሆነ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ይህንን ተከትሎም አንዳንድ የስደተኞች ጠበቆች በተለያዩ የስደተኞች ማጎሪያ ያሉ ደንበኞቻቸው በኢሚግሬሽን ኦፊሰሮች ወደ ሊቢያ ዲፖርት ሊደረጉ እንደሆነ እንደተነገራቸው ጠቁመው ጉዳዩን ዛሬ ረቡዕ ሜይ 7 ወደ ፍርድ ቤት ይዘውት ሄደዋል።
ጠበቆቹ እንደሚሉት ደንበኞቻቸው ከቪየትናም፤ ላኦስና ፊሊፒንስ እንደሆኑና በፍጹም ከአህጉሩም ሆነ ከአገሩጋ ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ጉዳዩን የያዙትና በማሳቹሴትስ የሚገኙት የዩ ኤስ ዲስትሪክት ዳኛ ብርያን ኢ መርፊ ታዲያ ማንኛውም ወደ ሊቢያ የሚደረግ ዲፖርቴሽን በፊት ስደተኞች ከህግ ፊት ቀርበው ጉዳያቸውን ማስረዳት እንዲችሉና በትክክልም ይህ ሶስተኛ አገር ለህይወታቸው እንደማያሰጋቸው መከራከር እንደሚችሉ ደምድመዋል።
ዳኛው አክለውም መንግስት ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ እንዲያቀርብ አዘዋል።