
በቨርጂንያ የአርሊንግተን ካውንቲ የስነጥበብ ኮሚሽን በየአመቱ የሚያወጣውንና ለአርቲስቶችና ለጥበብ ተቋማት የሚሰጠውን የድጋፍ ገንዘብ ማመልከቻ መቀበል ጀምሯል። ካውንቲው በዚህ የድጋፍ ፕሮግራም ለግለሰብ አርቲስቶች እስከ 15ሺህ ዶላር ድረስ ድጋፍ ያደርጋል። ለጥበብ ተቋማት ደሞ እንደ ማመልከቻቸውና አስፈላጊነቱ እየታየ ድጋፍ ያገኛሉ።
የዚህ የግለሰቦች የገንዘብ ድጋፍ ማመልከቻ ታዲያ ኤፕሪል 29 ጀምሮ ክፍት ሲሆን እስከ ጁን 18 ድረስ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ታውቋል። በዚህ ዙር 4 አርቲስቶች እያንዳንዳቸው 15ሺህ ዶላር የምሚያገኙ ይሆናል። ይህ ድጋፍ ለአርቲስቶች በተለይም ሰዎች በስነጥበብ የተሻለ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚረዱ፤ በአርሊንግተን ካውንቲ የጥበብ ክህሎት እንዲዳብር ለምሚያደርጉ፤ የባህልና ማህበረሰብ አቀፍ ለሆኑ የጥበብ ስራዎች እንዲሁም ትርጉም ያላቸውን ማህበረሰባዊ ግንኙነቶች ለሚፈጥሩ አርቲስቶች ይሰጣል ተብሏል።
የውድድሩ ዳኞችም በዋናነት ለፍትሀዊነት (equity)ና ለወጣቶችና ታዳጊዎች የአዕምሮ ጤና ለሚሰሩ ማመልከቻዎች የተሻለ ነጥብ እንደሚሰጥ ታውቋል። በዚህ ውድድር ያሸነፉ ባለሞያዎች ከጁላይ 1 2025 ጀምሮ እስከ ጁን 30 2026 ፕሮጀክታቸውን ማጠናቀቅ አለባቸው።
ስለዚህ ፕሮጀክት ማስረጃና ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም ለሐሙስ ሜይ 8 የተዘጋጀ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ለመሳተፍ ይህን ሊንክ መጫንና መመዝገብ ይቻላል። ስለ ድጋፉ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ደሞ የካውንቲውን ሙሉ ሪፖርት ይህን በመጫን ማንበብ ይችላሉ።