@ethiopique202 - 2025-06-16T211455.780

ኢትዮጲክ – ዱኒያ እንግዳችን ስለሆንሽ በቅድሚያ እናመሰግናለን። እንኳን ለመጽሀፍ ምርቃትሽ አደረሰሽ።
 
ዱኒያ – እኔም በጣም አመሰግናለሁ። እንግዲህ አሁን በማድረግ ላይ ያለሁት pre-launch (ቅድመ-ምርቃት ማስተዋወቂያ) ነው። ያ ማለት እንግዲህ አንዳንድ ዝግጅት ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን በአካል እና በኦንላየን እያስተዋወቅኩ ነው። ምርቃቱን እንግዲህ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ጋር በመሆን በደንብ እያቀድንበት ነው።

ኢትዮጲክ – እስቲ እንግዲህ በቀጥታ ወደ መጽሃፍሽ ከመሻገራችን በፊት ዱኒያ ማናት ለሚሉ እራስሽን አስተዋውቂልን

ዱኒያ – ዱኒያ መኮንን ተገኝ እባላለሁ። የሕግ ባለሞያ ነኝ። የሴቶች እና የሰብዓዊ መብት ሥራዎችን ስሰራ ቆይቻለሁ። 2007(እ.ኤ.አ) ነው ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በህግ የተመረቅኩት። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በሰብዓዊ መብት የማስተርስ ዲግሪ ይዣለሁ። የማዕረግ ተመራቂም ነበርኩኝ። ከዛ በኋላ እዚህ መጥቼ በጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ የህግ ማዕከል መጥቼ የአሜሪካ የደህንነት ህግ እና የሴቶች ፖሊሲ ላይ ሌላ ማስተርስ እና የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ። እዚህም በማዕረግ ነው የተመረቅኩት። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ከሥራዬ ጋር በተገናኙ ከጦርነት እና ፖሊሲ ዙሪያን ጨምሮ ብዙ የምስክር ወረቀቶችም አሉኝ።…

በተመሳሳይ ከብዙ ተቋማትም ጋርም አብሬ ሰርቻለሁ። ከዛ ውጭ በተባበሩት መንግስታት የደህነንት እና የጸጥታ የምስክር ወረቀቶችም አሉኝ… ለመንግስታቱ ድርጅት ሥሰራ ያገኘኋቸው። በተጨማሪም በህግ ቢሮዎች ውስጥም የህግ ረዳት ሆኜ የሰራሁ ሲሆን አሁን ደግሞ የራሴን የህግ ምርምርና የምክር አገልግሎት ተቋም ከፍቻለሁ።

ኢትዮጲክ – የመሰረትሽው መኮንን ተገኔ (MT Legal) ተቋም በዋናነት ምን ላይ ነው የሚሰራው?

ዱኒያ – ኤም.ቲ ሌጋል የህግ ምርምር እና የማማከር አገልግሎትን በአባቴ ስም ነው ያቋቋምኩት። የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው። እኔ እዚህ ሀገር መጥቼ ፕሮጀክት ማኔጅመንት የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ እና ከዚህ በመነሳት በጻፍኩት የህግ መጽሀፍ ላይ እንዳለው ዓይነት የተለያዩ አጋዥ(tools) እና ፕሮጀክቶችንም መቅረጽ ላይ ያተኩራል። ከዛ ውጭ የህግ ጥናቶችን እናደርጋለን።…አሁን ደግሞ በኒውዮርክ ባር (የጥብቅና ፈተና) ለመፈተን እየተጠባበቅኩ ነው። ፈተናው ትንሽ አስቸጋሪ ነው። እንግዲህ ጠበቃ እስክሆን ድረስ ማኅበረሰባችንን ማገልገል የምችላቸውን፤ የሚፈቀዱልኝን ቦታዎች አገለግላለሁ። ለምሳሌ በአማርኛ እና የእንግሊዝኛ የትርጉም ሥራዎችን እሰራለሁ። የህግ ሰነዶችንም እተረጉማለሁ። ከዛ ውጭ በጠበቆች ተቀጥሬ የህግ ሰነዶችን እና የመሳሰሉትን ሥሰራ ስለቆየሁ ለዛ ነው ያንን ሥራ በድርጅት ስር ለማድረግ የከፈትኩት።

 
ኢትዮጲክ – ወደ መጽሀፍሽ እንመለስ፤ መጽሀፍሽ ‘አጀንዳ 2063 የአሁኑ የአፍሪካ ሴቶች ድምጽ’ የተሰኘ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሀፍ ነው። የመጽሀፍሽ ዐቢይ ትኩረት ምንድነው?

ዱኒያ – መጽሃፉ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ራዕይ ላይ ያተኮረ ነው። ያው አፍሪካ የራሷ አጀንዳ አላት። እንደአፍሪካም ይሄንን ቀርጸን እነዚህን ነገሮች እናሟላለን ብለን ሀገራት አቅደዋል። የእኔ መጽሀፍም ህበረቱ ያንን ህልም ወይም ግብ በተለይም በሴቶች ዙሪያ ያስመዘገበውን ነው የገመምገመው። በሴቶች ዙሪያ ያተኮረው ግብ ስድስት (Aspiration 6) ይባላል። ይሄ ግብ ግን በእኔ ግምገማ እና አመለካከት በተለይ ለመጀመሪያው አስር ዓመት እስከ 2023-2023(እ.ኤ.አ) አዲስ ዕቅድ አውውጥተዋል። ስድስት ሀገራትን ያማከለ ግምገማ ነው። ሀገራቱ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ዩጋንዳና ናይጄሪያ ናቸው። በእነዚህ ሀገራቶች ውስጥ ጎልተው የታዩና ያልተፈቱ ያልኳቸው ችግሮች ከሴቶቹ ጋር በመነጋገር፣ በራሴ ጥናት በማድረግ፣ ከህግ በተጨማሪም ከህግ ባለሞያዎች ጋር በመነጋገር፤ እንዲሁም ሀገር ውስጥ እና የአለም አቀፍ ጥናቶች ላይ ተመርኩዤ ነው የጻፍኩት። መጽሃፉ የወደፊቱ ላይም ያተኮረ ነው። ያ ማለት እንዴት አድርገን የሚመጣውን የሁለተኛ የትግበራ ዕቅድ እናስተካከል እና እንፈጽም? እንዴት ይፈታ የሚለው ነው ዋናው ትኩረቱ። እንግዲህ ላለፉት 10 ዓመታት ከ2015 (እ.ኤ.አ) ነው እነዚህን ጥናቶች ሥሰራ የነበረው። …

ኢትዮጲክ – በዋናነት በስድስቱ ሀገራት ያየሻቸው የሴቶች ተግዳሮት እና ክፍተቶች ምንድናቸው?

ዱኒያ – በሁሉም ሀገራት የሚለያዩ ጉዳዮች አሉ። በተለይ እንደናይጄሪያ ያሉ ሀገራት ያናገርኳቸው በፍርድቤት አካባቢ የሚሰሩ ባለሞያዎችን ነው። በተለይም ጉዳዩ በግርዛት ዙሪያ ስለነበር አንደኛ ስላለው አጉል ልማድ ሁለተኛ ደግሞ በህግ አፈጻጸሙ ውስጥ ስላሉ በቦታው ያሉ ዳኞችን ነው ቃለ-መጠይቅ ያደረግኩት። በተጨማሪም በራሳቸው የተሰሩ ጥናቶችም አሉ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ አለም አቀፍ የሆኑ በመንግስታቱ ተቋማት የተሰሩ ጥናቶችም አካትቻለሁ። እንግዲህ ከሴቶቹ የራሳቸውን የህይወት ተሞክሮ ማግኘት፤ እንዲሁም ደግሞ ከፍርድ ቤቶቹ ደግሞ ያለውን ሁኔታ እና ፖሊሶች ህጉን በአግባቡ ያስከብራሉ ወይ? በሚል ያነጋገርኳቸው ሰዎች አሉ። በተጨማሪም ከጉዳዩ ጋር በቅርበት የሚሰሩ ባለሞያዎችና በችግር ምክንያት እዚህ ሀገር የመጡ ሴቶችንም አነጋግሬያለሁ።… ስለሱዳንም ከሱዳን እዚህ ሀገር የመጡ ሰዎችን በማነጋገር ነው የተረዳሁት። … በኢትዮጵያም የማውቃቸውን የተቋማት ሥራዎችን አካትቻለሁ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ሥራ የተለያዩ ሀገራት ያሉ ተቋማቶችንም ሥራዎች አካትቻለሁ።
በዋናነት ያየኋቸው ተግዳሮቶች እንግዲህ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ችግር አለ። በተለይ ባህሉን የሚፈጽሙ ሰዎች መካከል ማለት ነው። ያ እንግዲህ የገቢያቸውም ምንጭም ጭምር ነው።ስለዚህ ይሄንን ለመከላከል እነዚህ ሰዎች በገቢ እራሳቸውን ማስቻል ለምሳሌ፦ የስራ ዘርፎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል።…ያ ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ በውውይት መልክ ልጆችን ማስተማር የመሳሰሉ መፍትሄዎችም ተቀምጠዋል። በተመሳሳይ በስድስቱም ሀገራት ያሉ ጎጂ ልማዶች አሁን አልተፈቱም። የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አሁንም ያለ ተግዳሮት ነው።…
 
 
ኢትዮጲክ – መጽሀፍሽን በዋናነት ማን እንዲያነበው በማሰብ ነው ያዘጋጀሽው?

ዱኒያ – እንግዲህ ሁላችን ከዚህ መጽሃፍ እንጠቀማለን ብዬ የማምን ሰው ነኝ። በተለይም ግን ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ። በመጽሃፉ እንዴት አድርገው የህግ ተጠያቂነትን ማምጣት እንዳለባቸው የሚያትቱ ነገሮች አሉ። ሌላው ደግሞ መጽሃፉ የህግ አካላት እና አቃቤ ህጎች እንዴት አድርገው ነው ማገልገል ያለባቸው የሚል መምሪያም አለው። ከዛ ውጭም የእምነት አባቶች እና የማኅበረሰብ ተኮር ተቋማትንም ይጠቅማል። ምክንያቱም አንዱ ማስተማሪያ መንገድ የህዝብን ንቃተ ህሊና መጨመር ነው።… ከዛ በተጨማሪ ደግሞ የአለም አቀፍ የህግ ተቋማትም የሴቶች የየፍትህ እና የፖለቲካ ተሳትፎን እዲጨምሩም ያግዛል። ለስነ ጾታ መምህራን ማስተማሪያም ይሆናል።…

ኢትዮጲክ – የመጽሀፍሽ ምርቃት መቼ ነው? ሰዎች መጽሀፉን እንዴት ያገኙታል?

ዱኒያ – መጽሀፉ እንግዲህ ነሃሴ ካልሆነም መስከረም ላይ ይመረቃል። ኦን ላየን ላይ መሸጥ ተጀምሯል። ነገር ግን ሰዎች ለምርቃቱ በአካል ቢገኙልኝ ደስ ይለኛል። በነገራችን ላይ መጽሀፉ በዩኒቨርስቲ ፕሬስ ነው የታተመልኝ። መጽሀፌ ወደ 22 የሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎችም የትምህርት ማገዣ (refrence) እንዲሆን አካተውታል። ሀርቫርድ፣ ፕሪስተን እና ጆርጅ ሜሰን የመሳሰሉት ዩኒቨርስቲዎች ቤተመጽሀፍት ውስጥ ይገኛል። ሰዎች እዛም ገብተው ሊያገኙት ይችላሉ። የሚገዙትም ለእኔ በጣም ይጠቅሙኛል። አዲስ ኤል.ኤል.ሲ ስለሆነ የመሰረትኩት ገቢው ተቋሙን ለማገዝ እና ብዙ ሥራዎችን ለመስራት ያግዘኛል።

ኢትዮጲክ – እንግዳችን ስለሆንሽ እናመሰግናለን።

ዱኒያ – እኔም ይሄንን ዕድል ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.