12/12/2024
Screen-Shot-2022-06-07-at-18.58.43

06/05/2022

ከዲሲ 147 ማይል ርቀት ላይ የምትገኘው ኦሽን ሲቲ በርካታ አዝናኝና አስተማሪ ነገሮችን በውስጧ የያዘች ከተማ ናት። እኛም ከሰሞኑ ሄደን ካገኘነው ልምድ ልናካፍላችሁ የተወሰኑ ነገሮችን ይዘን መተናል።

ኦሽን ሲቲ ለመድረስ ቢያንስ 2 ሰዓት ተኩል የመኪና ጉዞ ይፈልጋል። ስለሆነም ወደዛ ለመሄድ ሲታቀድ ለሁለት ወይንም ከዛ በላይ ላለ ቀን ለማሳለፍ አቅዶ መሄድን እንመክራለን። አለበለዚያ ግማሽ ቀን በመንገድ ብቻ ያልቃል።

ኦሽን ሲቲ በጣም ብዙ ሆቴሎች እዚህም እዛም አለ ግን ዋጋቸውና ጥራታቸው እጀግ የተለያየ ነው። እኛ የተለያዩ ሆቴሎችን ዋጋና ጥራት ከ booking.com , expedia.com , trivago.com , airbnb.com እና hotels.com ላይ አወዳድረን ለቤተሰብ ከነልጆች ጥሩ ነው ያልነውን ሆቴል ኪስ በማይጎዳ ዋጋ አግኝተን ተከራይተናል። እዛ ከደረስን በኋላ ያደረግናቸውን 9 ነገሮች ደግሞ እነሆ

  1. ቢች ዳር መዝናናት – በተለይ ልጆቻችሁን ይዛችሁ የምትሄዱ ከሆነ የውቅያኖሱ ዳርቻ አሸዋው ላይ ዘና ፈታ ለማለት አሪፍ ነው። የሞገዱ ድምጽ፤ የወፎቹ ጫጫታና የንፋሱ ድምፅ ኑሮን ለመርሳት አሪፍ ነው። ልጆች በአሸዋ የተለያዩ ጨዋታዎችን መጫወት ይችላሉ። የኛ ልጆች ቀኑን ሙሉ ጉድጓድ ሲቆፍሩ ልባቸው ውልቅ ብሎ ነው ቤት የገቡት። በበጋ ውሃው ስለሚሞቅ መነከር፤ መዋኘት ወይንም ውስጡ ተዘፍዝፎ ጀርባን በሞገዱ ማስመታት ይቻላል። ሁለተኛው ቀን ላይ አየሩ ቀዝቃዛና በጣም ነፋሻ ስለነበር እንደመጀመሪያው ቀን አልተዝናናንም።
  1. ምግብ – ሁሌም እንደዚህ አይነት ቦታ ስንሄድ ለሙሉ ቤተሰብ ምሳና እራት የሚሆን አገልግል አዘጋጅተን ፍሪዝ አድርገን ነው የምንሄደው። እዛ እንደደረስንና ሆቴላችንን እንደተረከብን የመጀመሪያ ስራችን ጥብስ ፍርፍራችንን አሙቀን መመገብ ነው። በባዶ ሆድ ልጅ ተይዞ ወደቢች አይወረድም። ያንን ከቀማመስን በኋላ ደሞ ከቤታችን ይዘነው የሄድናቸውን ስናኮችና ውሃ በየመሃሉ እንካፈላለን። ለእራታችን ከቢች መልስ ቦርድወክ ላይ ካሉት ፒዛ ቤቶች አንዱ ከሆነው ካሩሶ ፒዛ አንድ አንድ ስላይስ ኢታሊያን ስታይል ፒዛ ቀጥለን ደሞ አንድ ማይል ተኩል ያህል በቦርድዎክ ላይ ዎክ አርገን ከዲፒን ዶትስ አይስክሪም ተቃምሰናል። አይስክሪም የምትወዱ ከሆነ መዓት አይነት አይስክሪም ቤቶች አሉ እንደምርጫችሁ። ሌላኛው በጣም ሰው የሚሻማበት ቤት ትራሸርስ ፍሬንች ፍራይስ የተባለ ቤት ነው። ብዙም የሚደንቅ ነገር የላቸውም።
  1. ኦልድ ታይም ፎቶ – የድሮ ፎቶ በተለያየ ስታይል መነሳት ለሚፈልጉ ጎብኚዎች የድሮ አልባሳት፤ መዋቢያዎች፤ ጥንታዊ ጠምንጃዎች እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። ጥንታዊ ነገሮችን የሚውድ ሰው ሊዝናናበት ይችላል።
  1. ቦርድ ወክ – አሽን ሲቲ ከታደረ በማታ ቦርድወክ ላይ ወክ ማረግ በጣም የሚያዝናናና ካሊፎርኒያን የሚመስል ደስ የሚል ስሜት አለው። የኦሽን ሲቲ ቦርድ ወክ በ3 ማይል ላይ የተዘረጋ ሲሆን በየማይሉ የተለያየ. ውበት ያላቸው ድርጊቶችን ያስተናግዳል። የልጆች መጫወቻ፤ ሙዚየም፤ የስጦታ ሱቆች፡ የዋናና የቢች መጠቀሚያ እቃዎች መሸጫ፤ የምግብ ቤቶች፤ የአይስክሪምና ካንዲ መሸጫዎች፤ የሳይክል መከራያ: የጥበብ ስራዎች.. ላይቭ ሙዚቃ.. ብቻ ምን አለፋችሁ.. ሁሉም ነገር አንድ ቦታ ድብልቅ ያለበት ቦታ ነው። ኦሽን ሲቲ ፊቱ ወደምስራቅ እንደመሆኑ እንደ ካሊፎርኒያ ውቅያኖስ ዳርቻዎች ሰንሴት እያየን መተከዝ ባንችልም ቦርድወኩ ግን ያንን የሚያስረሳ ድባብ ይፈጥራል።
  1. አሳ ማጥመድ – አሳ በማጥመድ መዝናናት ለሚፈልጉ የሜሪላንድ የኮስታል አሳ ማጥመጃ ፍቃድ በ7$ አውጥተው ከፈለጉ ከፒየሩ ላይ ካልሆነም በኢንሌት ፓርኪንጉ በኩል ባሉት ቋጥኝ አለቶች በኩል ማጥመድ ይችላሉ። ብቻዎትን ሰው ሳይረብሽዎት አሳ ማጥመድ ከፈለጉ ደግሞ ጉግል ማፕ ላይ 9th ST fishing Pier ብለው ብዙ ሰው የማያዘወትራት ሰዋራ ቦታ ላይ በሰላም ማጥመድ ይችላሉ። አሳ ሲያጥምዱ ታዲያ የሜሪላንድን ህግ ማክበርዎን እንዳይዘነጉ።
  1. ካይት – በተለይ ልጆች ይዘው የሚጓዙ ከሆነና የአየር ሁኔታው ከፈቀደ ካይት እዛው ቦርድዎክ ላይ ካለው ካይት-ሎፍት ገዝተው ልጆችዎን ማዝናናት ይችላሉ። እውነቱን ለመናገር ካይት ማብረር ለአዋቂም የሚያዝናና ስራ ሆኖ አግኝተነዋል።
  1. ትሪምፐርስ ራይድ – ትሪምፐርስ ራይድ ያው እንደማንኛውም አሚውዝመንት ፓርክ አዝናኝ፤ በህዝብ የተጨናነቀና ውድ ቦታ ነው። ልጆች ካሏችሁ ደሞ ከሱ ሌላ ምንም አይታያቸውም። አብዛኛዎቹ ታዋቂ የአሚውዝመንት ፓርክ መጫወቻዎች.. ስሊንግሻትን ጨምሮ አላቸው። በሰው ከመጨናነቁ ውጪ ቦታው አዝናኝ ነው።
  1. ሪፕሊ-ብታምኑም ባታምኑም (Ripley’s – Believe it or not) – ይህ የአቶ ሪፕሊ የድንቃድንቅ ሙዚየም ማንኛውም ሰው ሊያየው የሚገባ የአለም አስገራሚ ፍጡራን የድሮ እቃዎች፤ የጥበብ ስራዎችና በዜና ብቻ የምናቃቸው 12 እግር ያላት ላም ተወለደች፤ 7 አይን ያለው ድመት ምናምን የመሳሰሉ ነገሮች የተሰባሰቡበት ቤት ነው። ካላያችሁት ስለማይገባ…አዛ ከሄዳችሁ ከምንም በላይ እንድታዩት። አዛ ስትደርሱ የመስታወት ጥምዝ ቤት (Mirror Maze) መግቢያ አብራችሁ እንድትገዙ ይጠይቋችኋል .. አንድ ላይ ወደ 26$ ገደማ ነው። የ መስታወት ጥምዝ ቤት (Mirror Maze) ከልጆቻችን ጋር ለመፍታት 2 ደቂቃ ነው የፈጀብን። ያን ያህል አጓጊም፤ ውስብስብም አስደናቂም አይደለም። ድጋሚ እድሉ ቢሰጠን መስታወት ቤቱን ትተን የሙዚየሙን ብቻ ነው የምናየው።
  1. ባኃ ራይድስ – ባኃ ራይድስ ከኦሽን ሲቲ ወጣ ብሎ ያለ 5-6 ትራክ ያለው የጎ ካርት መወዳደሪያ ቦታ ነው። ልጆች ካሏችሁ በጣም የሚዝናኑበት ቦታ ነው፡፡ ልጆች ባይኖራችሁም ለአዋቂም የሚያዝናና ቦታ ነው። ወጣት እያለን ብናገኘው ሁለተኛና ሶስተኛ ዴት የምንሄድበት ቦታ ነው ባኃ ራይድስ። ባኃ ራይድስ የተለያዩ ቅናሾች አሉት .. ልጆቻችን ከ 3 ራይድ በኋላ በቃን ብለው ትኬቱ ሪፈንድ ስለማይደረግ በግድ ተጨማሪዎቹን አስነድተን ነው የወጣነው። ከመግዛታችሁ በፊት ምን ያህል እንደምትገዙ አስቡበት። በፍፁም አንድ ቲኬት እንዳትገዙ ከብዛት ይቀንሳል።

እኛ ይህን አድርገን ተመልሰናል። እዚህ ከዘረዘርናቸው በላይ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ መዝናኛዎች አሉ እንደ ካይት ሰርፊንግ፤ ቡሌት ቦትስ፤ ወተር ፓርኮች፤ ሃይኪንግ፤ እና ሌሎችም።
እናንተ የምታካፍሉን ሌላ ልምድ ካላችሁ ወይንም ጥያቄዎቻችሁን በኢሜል ላኩልን።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት