
በዋሽንግተን ዲሲ የ911 የስልክ ጥሪ አገልግሎት እያደር እየተበላሸ እንደመጣና በኤጀንሲው ግድፈቶች ምክንያት የሰው ህይወት እየጠፋ እንደሆነ በቅርብ የወጣው የኦዲት ሪፖርት ያሳያል። በኦዲቱ ላይ እንደታየውም ታዲያ ዋነኛው የመስሪያ ቤቱ ችግር እንደ ከሪማ ሆምስ ያሉ አመራሮቹ ላይ እንደሆነ ተጠቁሟል።
በመስሪያቤቱ ሰራተኞች ግድፈትና ቸልተኝነት ከጠፉት ህይወቶች በኦገስት 18፣ 2019 ኬኔዲ ስትሪት ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ለህልፈት የተዳረጉት የ9 አመቱን ያፌት ሰለሞንና የ40 አመቱን ፍፁም ከበደን ተጠቃሽ ናቸው።
የዲሲ 911 የስልክ ጥሪ ማዕከልን ጉዳዬ ብሎ የሚከታተለው የዴቭ ስታተር ጥንቅር እንደምሚያሳየው የ911 ጥሪ ተቀባዮች በአደጋው ወቅት መረጃውን ለእሳት አደጋ ለማሳወቅ 4 ደቂቃ ፈጅቶባቸዋል። ይህን ተከትሎም የእሳት አደጋ ተከላካዮች በተገቢው ሰዓት አልደረሱም።
ከነያፌት አሳዛኝ አደጋ በተጨማሪ በ2020 3 ሰዎች ፖቶማክ ወንዝ ውስጥ በመስመጥ ለህልፈት ሲዳረጉ 911 ስልክ ተቀባዮች የነፍስ አድን ሰራተኞችን የተሳሳተ ቦታ በመላካቸው በተገቢው ሰዓት ሊደርሱላቸው አልቻሉም።
በተመሳሳይ ማርች 14 2022 ዴቪድ ግሪፊን የተባለ ግለሰብ ከድልድይ ዘሎ ለህልፈት ሲዳረግ የ911 ጥሪ ተቀባዮች ለፖሊስና ለነፍስ አድን ሰራኞች ትክክለኛ ቦታውን ባለማሳወቃቸው ሊደርሱለት እንዳልቻሉ ተዘግቧል።
ይህ መስሪያ ቤት ይህን ሁሉ ችግር እንዳስተናገደ በኦዲት ቢገኝበትም ታዲያ ከንቲባ ሙሪየል ባውዘር የዚህ ሁሉ ችግር መነሻ ናቸው የተባሉትን ከሪማ ሆምስን በድጋሚ ሾመዋቸዋል።
ነዋሪዎችና ጉዳዩ ያገባናል ያሉ ሰዎች ከሪማ ሆምስን ስለ ፕላናቸውና አስተዳደራዊ ችግሮች ተብለው የቀረቡ ችግሮችን ለመፍታት ሲወተውቱ ከርመዋል። ይህን ተከትሎም ከሪማ ሆምስ ነገ ከዋርድ 4 ነዋሪዎች ጋር ለመምከር ቀጠሮ ይዘዋል። የዋርድ 4 ነዋሪዎች የ911 ጉዳይ የሁላችሁም ጉዳይ ነው። ሂዱና ምከሩ። በአካል መሄድ ለማይችሉ በዙም እንዲክካፈሉ ተመቻችቷል። ከስር ያለውን ምስል ላይ ባለው አድራሻ በአካል ወይንም በዙም መካፈል ይችላሉ።
