በዘንድሮው ምርጫ ሜሪላንዶች ከመሪዎቻቸው በተጨማሪ የተወሰኑ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ድምጻቸውን ይሰጣሉ።ከነዚህም አንዱ የማሪዋና/ካናቢስን በመዝናኛነት መጠቀም መፍቀድን ይመለከታል። ይህ በ4ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተቀመጠ ጥያቄ ላይ እድሚያቸው ከ21 ዓመት በላይ የሆኑ ግለሰቦች በሜሪላንድ ስቴት ውስጥ ማሪዋና/ካናቢስ በመዝናኛነት እንዲጠቀሙ ፍቃድ እንዲኖር ወይንም እስካሁን እንዳለው በወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር ሆኖ እንዲቀጥል መራጮች በድምጽ ይወስናሉ።
እስካሁን ሜሪላንድ ውስጥ ማሪዋና የህክምና ፍቃድ ያላቸው ሰዎች ብቻ ያለተጠያቂነት ይጠቀሙት ነበር። ይህ ህግ በመራጮች ከተሻረ ከጁላይ 2023 ጀምሮ ማንኛውም ዕድሜው ከ21 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ያለማንም ጠያቂነትና ከልካይነት ማሪዋናን ለመዝናኛነት መጠቀም ይፈቅዳል ይህም ህግ ሆኖ በሜሪላንድ ህገ-መንግስት ውስጥ ይካተታል።