ጌይተርስበርግ፣ ሜሪላንድ –
የሞንትጎመሪ ካውንቲ የፖሊስ ዲፓርትመንት ዲሴምበር 8 በኒውኃምሻየር ጎዳና በተፈፀመ የግድያ ወንጀል በተያያዘ ተጠርጣሪ ነው ያሉትን የ31 ዓመቱን የሲልቨር ስፕሪንግ ቶሬይ ሙርን በቁጥጥር ስር አውለው ክስ መስርተዋል።
ግድያው የተፈፀመው በኒው ሃምፕሻየር ጎዳና 11100 ብሎክ ውስጥ ባለው የሼል ጋዝ ማደያ (Dash In Convenience Store) ነው። ፖሊስ በእለቱ ከከሰዓት 3፡30 ላይ የስልክ ጥሪ ደርሶት በቦታው ሲደርስ በጋዝ ማደያው ሱቅ ውስጥ ሰው በጥይት ተመቶ ያገኙ ሲሆን ይህ ሰውም በኋላ ላይ በተደረገ ማጣሪያ በማደያው ተቀጥረው የሚሰሩት የ61 አመት አመት አዛውንት የሆኑት አቶ አያሌው ወንደሙ እንደሆኑ አሳውቋል፡፡ በፖሊስ ምርመራ መሰረት በሙርና በአቶ አያሌው መኃል መነሻው ምን እንደሆነ ያልታወቀ እሰጥ አገባ እንደነበራቸውና በኋላም ይህ እሰጥ አገባ ወደ አካላዊ ግጭት (ድብድብ) ተቀይሮ ተጠርጣሪው ሽጉጥ አውጥቶ በሟች ላይ በርካታ ጊዜ እንደተኮሰባቸውና ለሞት እንደዳረጋቸው ፖሊስ አሳውቋል።
ፖሊስ ተጠርጣሪን ተከታትለው ይኖርበታል ወደተባለው ኢንክሌቭ አፓርታማ የመበርበሪያ ወረቀት ይዘው በመሄድ በቤቱ ባደረጉት ፍተሻ ሌላ መበስበስ የጀመረና ማንነቱ ያልታወቀ ሰው ሬሳ እንዳገኙ አክለው ተናግረዋል። ተጠርጣሪው ሙር በኋላ ላይ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃሉ የበሰበሰው ሬሳ የፍቅረኛው እንደሆነና በሞተችበት ወቅትም የ8 ወር ነፍሰጡር እንደነበረች ተናግሯል።
የዚህች ሟች ሬሳ ለተጨማሪ ምርመራ ወደባለሞያዎች የተላከ ሲሆን ፖሊስ የሟችን ማንነትና ሌሎች ጉዳዮች ወደፊት ያሳውቃል።
በዚህ ምርመራ ላይ ተጨማሪ መረጃ ያላቸው ሰዎች በስልክ 240-773-5070 ወይንም በ 1-866-411-8477 ደውለው እንዲጠቁሙ ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል።
ለሟቾች ነፍስ ይማር