12/12/2024
HAPPY (8)

የነገ ማክሰኞ ጁን 27 ለሚደረገው የሞንጎምሪ ካውንቲ የትምህርት ቦርድ ስብሰባ በርካታ ሰዎች ለመሳተፍ ፍላጎት በማሳየታቸው የካውንቲው የህዝብ ትምህርት ቤቶች የደህንነት እርምጃዎችን ወስጃለሁ ሲል በትዊተርና በኢሜይል አሳውቋል።


ከነዚህ የደህንነት እርምጃዎች አንዱ ስብሰባው በሚደረግበት የካርቨር የትምህርት ማዕከል ህንጻ ለተፈቀደላቸውና ንግግር አድራጊዎችና ተጋባዥ እንግዶች ብቻ መግባት እንደሚቻል ተነግሯል።

ማንኛውም የተቃውሞም ይሁን የድጋፍ ሰልፈኞች በህንጻው በስተምስራቅ በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ላይ ብቻ እንዲሰበሰቡ ተብሏል። በተጨማሪም ሁሉም የትምህርት ቦርድ ስብሰባዎች በዩቲዩብና በኬብል (MCPS-TV on Comcast Channel 34 (HD 1071), Verizon Channel 36, RCN Channel 89.) እንደሚተላለፉ ተጠቁሟል።

ይህ ዜና በአንዳንድ የካውንቲው ነዋሪዎች ዘንድ ተቀባይነትን ያላገኘ ሲሆን በዚሁ የትዊተር ልጥፍ ስር ዜጎች ብሶታቸውን አሰምተዋል። ከነዚህም ውስጥ በአንዱ አካውንት ይህ ውሳኔ የሜሪላንድን የመንግስት ስብሰባዎች ለዜጎች ክፍት መሆን አለባቸው የሚለውን ህግ ይጥሳል ብለዋል።

ሌላኛዋ ተቃዋሚ ደሞ በስብሰባው የሌላኛው ወገኖች ተመርጠው እንዲገቡ ፍቃድ ሊሰጣቸው እንደሚችልና የካውንስሉ አባላት ራሳቸው የራሳቸውን ሰዎች ሰብስበው ድጋፍ በማሰማት የተቃዋሚዎችን ድምጽ እንዲዋጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት