ነገ ሐሙስ ኦገስት 31 አለም አቀፍ የኦቨርዶዝ አዌርነስ ቀን ወይንም በመድሃኒት/አደንዛዥ እጽ ከመጠን በላይ በመውሰድ ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች የሚታሰቡበት ቀን ነው። ምንም እንኳ በርካታ የኛ ልጆች የሱስና የአዕምሮ ህመሞች ተጠቂዎች ያሉ ቢሆንም በኛ ማህበረሰብ ውስጥ በዝምታ ከምናልፋቸውና ብዙ ከማናወራቸው ጉዳዮች ነው ብለን እናስባለን። አንዳንድ ነገሮች የኛን ማህበረሰብ የሚነኩ ስለማይመስለን ብዙ ቤተሰቦች ይዘናጋሉ። የኢትዮጲክ ባልደረቦችም ይህን ቀን እንዲሁ ማሳለፍ ትክክል መስሎ ስላልተሰማን ይህንን ቀን በያለንበት የአንጋፋዋ ጋዜጠኛ የትዝታ በላቸውና ባለቤታቸው አቶ ቦጋለ በላይነህን ልጅ ወጣት ቢያ በላይነህን አስበን እንውላለን። ወጣት ቢያ በጣም በትምህርቱ ጎበዝ ሰው ሁሉ የሚቀናበት ነበር ሆኖም በለጋነቱ የድብርትና ባይፖላር ህመም ተጠቂ በመሆኑ ለህክምና በሚወስዳቸው መድኃኒቶች ምክንያት ለተለያዩ ሱሶች ተዳርጎ ነበር። በመጨረሻም ይህ ሁሉ ድርብርብ ከኮሮና ጋር ተጨማምሮ ለህልፈት እንዲዳረግ አድርጎታል። ሙሉ ታሪኩን ይህን ሊንክ በመከተል የሄለን ሾው ላይ ማየት ይችላሉ።
ወላጆቹ ታዲያ ይህ ሲፈጠር ዝም ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። ቢያ በላይነህ ፋውንዴሽን የተባለ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት አቋቁመው በአካባቢያችን ያሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከአዕምሮ ህክምናጋ በተያያዘ የመረጃ ክፍተትን ለመድፈን እየሰሩ ይገኛሉ። እስካሁንም ይህ ድርጅት በአማርኛና በሌሎች የአገርቤት ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጡ ባለሞያዎችን ዝርዝር አዘጋጅተዋል። ይህን ሊንክ ተጭነው በመሄድ ይህን ዝርዝር ማግኘት ይችላሉ። ወይዘሮ ትዝታን ዛሬ በስልክ አውርተናቸው እንደነገሩን ታዲያ ፋውንዴሽኑን እሳቸው ቢጀምሩትም በቂ የሰው ኃይል ስለሌለው በተለያየ ዘርፍ የሚያግዙን በጎ ፈቃደኞች እንፈልጋለን ብለውናል። እርስዎም ሳይሰለችዎት እስከዚህ ድረስ ካነበቡ በእርግጥም ጉዳዩ ጠቃሚ ነው ብለው አስበዋልና እባክዎ በዚህ ሊንክ ተመዝገቡና አግዟቸው።
የኢትዮጲክ መልዕክት
የሚሰራ ኮሚውቲ የለም ብሎ ሁሌ ከማማረር የሚሰሩትጋ እየሄዱ ምን እናግዝ ብለን መጠይቅን ባህል እናርግ። ከተቋቋሙት ማህበሮች ምንም ሳንጠብቅ እኛ በአቅማችን የምንችለውን እናርግላቸው እንላለን።
በዲሲ ሜሪላንድና ቨርጂንያ ያሉ በርካታ አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘትና የኢትዮጲክ ዲጂታል ጋዜጣ በኢሜይልዎ እንዲደርስዎት ይህን ሊንክ ተጭነው ይመዝገቡ
ለዲሲ የአመቱ ምርጥ በጎ ፈቃድ ጥቆማ መስጠት ተጀመረ
የዲሲ ከንቲባ ሚውሪየል ባውዘር ማህበረሰባቸውን በበጎ ፍቃድ በማገልገል ላቅ ያለ ሚና ተጫውተዋል ለሚሏቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕውቅናና ሽልማት ለማበርከት እንዳቀዱ ዛሬ አሳውቀዋል። ነዋሪዎች ይህ ሽልማት ይገባቸዋል የሚባሉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንዲጠቁሙም ጥሪ አቅርበዋል። እናንተም እኛን ኢትዮጲክን ጨምሮ ሌሎች ይገባቸዋል፤ የበጎ ፍቃድ አገልግሎታቸው አርኪ ነው የምትሏቸውን ግለሰቦች ወይንም ተቋማት ካሉ ከስር ባለው ሊንክ ገብታችሁ ጥቆማችሁን ማስገባት ትችላላችሁ።