12/12/2024
Add-a-heading3

ከሰሞኑ የአርሊንግተን ቨርጂንያ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ የ73 ዓመት አዛውንት የሆኑት ወይዘሮ አቦነሽ ባሳለፍነው እሁድ ኦገስት 27 2023 ዓም ታስረው በነበረበት የአርሊንግተን ካውንቲ እስር ቤት እንዳረፉ ማስታወቁን ዘግበን እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኢትዮጲክ ባልደረቦች ዜናው ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የሚመለከታቸውን አካላት በስልክም በኢሜይልም ለማናገር የሞከሩ ሲሆን እስካሁን በጉዳዩ ላይ በከፊል ምላሻቸውን የሰጡን የአርሊንግተን ካውንቲ ፖሊስ ኮሚውኒኬሽንና ኮሙኒቲ ኢንጌጅመንት ባለሞያ የሆኑት ኦፊሰር ኤሚ ሚኃን ብቻ ናቸው፡፡ ለኦፊሰር ኤሚ ካቀረብንላቸው ጥያቄዎች አብዛኞቹን ወደ ቨርጂንያ ፍርድ ቤት የተመሩ በመሆኑ አጥጋቢ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄና መልሱን እነሆ

ኢትዮጲክ፡ የወይዘሮ አቦነሽ የአዕምሮ ጤና ምን ይመስል ነበር? የአዕምሮ ጤና መጓደል ምልክቶች አሳይተው ነበር?

ኦፊሰር ኤሚ፡ ይህ በምርመራ ላይ ያለ ጉዳይ ስለሆነና በእስር ላይ ያለ ሰው መረጃ ስለሆነ መልስ መስጠት አንችልም፡፡

ኢትዮጲክ፡ ወይዘሮ አቦነሽ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መግባባት ይችላሉ? ካልቻሉስ አስተርጓሚ ቀርቦላቸዋል? አስተርጓሚ ከቀረበላቸውስ ምን ከሚባል ድርጅት ነው የቀረበላቸው?

ኦፊሰር ኤሚ፡ በእስር ላይ ስላለ ሰው መረጃ የመስጠት ግዴታ ስለሌለብን መልስ ከመስጠት እንቆጠባለን፡፡

ኢትዮጲክ፡ ወይዘሮ አቦነሽ የታሰሩበትን ፋይል ፎቷቸውን ጨምሮ ማግኘት ይቻላል?

ኦፊሰር ኤሚ፡ የታሰሩበት ፋይልና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች በዚህ ሊንክ ከፍርድ ቤት ድረ ገጽ ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡ ፎቷቸውን ለFOIA (Freedom of Information Act) team ጥያቄያችሁን አስገባላችኋለሁ፡፡ (ከ2 ቀን በኋላ ፎቷቸውን በኢሜይል ልከውልናል)

ኢትዮጲክ፡ የፍርድ ቤት ኬዛቸውን ለማግኘት የኬዝ ቁጥራቸውን ማግኘት ይቻላል?

ኦፊሰር ኤሚ፡ በዚህ ሊንክ ሄዳችሁ ሙሉ ስማቸውን አስገብታችሁ ማግኘት ትችላላችሁ

ኢትዮጲክ፡ የቡኪንግ ቁጥራቸውንስ ሊሰጡን ይችላሉ?

ኦፊሰር ኤሚ፡ በእስር ላይ ስላለ ሰው መረጃ የመስጠት ግዴታ ስለሌለብን መልስ ከመስጠት እንቆጠባለን፡፡

ኢትዮጲክ፡ ወይዘሮ አቦነሽ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የህግ ባለሞያ አናግሯቸዋል? በጠበቃ ተወክለዋል?

ኦፊሰር ኤሚ፡ መረጃውን በፍርድ ቤቱ ድረገጽ ላይ ገብታችሁ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ኢትዮጲክ፡ ወይዘሮ አቦነሽ የአሜሪካ ዜጋ ነበሩ? ካልሆነ የዜግነቻው ሁኔታ ምን ነበር?

ኦፊሰር ኤሚ፡ ይህን ጥያቄ እኛ መመለስ አንችልም፡፡ የአሜሪካ ስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው U.S. Immigration and Customs Enforcement’s (ICE) ን ጠይቁ፡፡

እኛም ተጨማሪ መረጃ ፍለጋ ከተላክንበት የፍርድ ቤት ድረገጽ በመሄድ ወይዘሮ አቦነሽ የመንግስት ጠበቃ እንደተመደበላቸውና ለኦክቶበር የፍርድ ቀጠሮ ላይ እንደነበሩ ተመልክተናል፡፡ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጲያ ኤምባሲ መረጃ ካለው ለመጠየቅ ስልክ ደውለን የሚያነሳ አላገኘንም፡፡

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት