ባሳለፍነው ረቡዕ ኦክቶበር 23 እኩለ ለሊት ገደማ በ1396 ፍሎሪዳ አቬኑ ኖርዝ ኢስት አቅራቢያ በሚገኘው የኤክሰን ጋዝ ስቴሽን ሰራተኛ የነበረችው ራህማ ሩሬ በጥይት ተመታ ሆስፒታል እንደገባችና ለህይወቷ አስጊ በሆነ ሁኔታ እንደምትገኝ ፖሊስ አስታውቋል።
ተጎጂዋ የቋንቋ ችግር እንዳለባትና በወቅቱ የኤቲ ኤም ማሽን ለመገልገል ወደጋዝ ስቴሽኑ ሱቅ ከገባ ደንበኛጋ መግባባት ባለመቻሏ ወደአምባጓሮ እንደተቀየረና ከአቅሟ በላይ ሲሆን ወደ ወንድሟ እንደደወለች ተነግሯል በዛው ጋዝ ስቴሽን የሚሰራው ወንድሟ ለኤንቢሲ 4 ተናግሯል። በኋላ ላይም ፖሊስ ለወንድምየው ደውሎ እህቱ በተተኮሰባት ጥይት እንደቆሰለች ነግሮታል።
እንደ ወንድየው ቃል ከሆን ራህማ ደረቷ ላይ በጥይት እንደተመታችና ተኳሹ በገንዘብ ማሳለፊያው ቀዳዳ ሽጉጡን አሾልኮ ጉዳቱን እንዳደረሰ ታውቋል።
ተጎጂዋ ራህማ በቅርቡ ከኤርትራ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እንደመጣችና የ5ወር አራስ ህጻን እናት እንደሆነ ተነግሯል።
የዲሲ ፖሊስ ጉዳቱን ያደረሰው ሰው አፍሪካ-አሜሪካዊ ወንድና ቁመቱ 5ጫማከ10 ኢንች እስከ 6 ጫማ እንደሚሆን በሰዓቱ ጥቁር ስካርፍ እንዳደረገና አፉ አካባቢ በስካርፍ እንደተሸፈነ፤ ረጅም ሌዘር ጃኬት እንዳደረገ፤ እንዲሁም ጥቁር ኮፍያና ጥቁር ጂንስ ሱሪ እንዳደረገ አስታውቋል።
ተጠርጣሪውን የሚያውቅም በስልክ 911 እንዲደውል ጠይቋል።