ባሳለፍነው ሳምንት በዚሁ በኢትዮጲክ በተደረገው ፖል ውጤት መሰረት በመጠይቁ ከተሳተፉ 51 ሰዎች 26ቱ ወይንም 51 ከመቶ የሚሆኑት በመጪው ፕሬዘደንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን እንደሚመርጡ ያሳወቁ ሲሆን 37 ከመቶ የሚሆኑት ለካማላ ኃሪስ ድምጻችንን እንሰጣለን ብለዋል። 10 ከመቶ ተሳታፊዎች እስካሁን ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ያልወሰኑ ሲሆን ሁለት ከመቶው ደሞ ለሌላ ተፎካካሪ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ጠቁመዋል።
ይህ ውጤት ኢትዮጲክ በኦገስት 5 በፌስቡክ ካወጣችውና 254 ሰዎች ከተሳተፉበት ፖል አንጻር ዶናልድ ትራምፕ በ5 ነጥብ ዝቅ ያሉ ሲሆን ካማላ ኃሪስ ደሞ የነበራቸውን 7 ነጥብ መልሰው አጥተዋል። በኦገስት 5ቱ ምዘና ዶናልድ ትራምፕ 56 ከመቶ ድምጽ አግኝተው የነበረ ሲሆን ካማላ ኃሪስ ደሞ 44 ድምጽ ላይ ነበሩ።
የኢትዮጵያውያን መራጮች ውጤት ታዲያ ታዋቂው የፒው ሪሰርች ካወጣው መመዘኛ በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን በብዛት ዴሞክራትን እንደሚመርጡ ካሳየበት መጠይቅ ውጤት ፍጹም ተቃራኒ እንደሆነ ያሳያል።
በተጨማሪም በፒው ሪሰርች ፖል ውጤት መሰረት 57% ላቲኖ መራጮች ለካማላ ኃሪስ ሲያደሉ 39% ብቻ ለዶናልድ ትራምፕ እንደሚመርጡ አሳውቀዋል።
በአካባቢያቸው ባሉ የሴኔትና የኮንግረስ ተወካዮች ምርጫ የትኛዎን ፓርቲ እንደሚመርጡ ለተጠየቁት ጥያቄ 53% አንባቢዎቻችን ሪፐብሊካንን 35% አንባቢዎች ዲሞክራትን ሲመርጡ 12 ከመቶ የሚሆኑ እስካሁን እንዳልወሰኑ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በሴፕቴምበር ወር ኢትዮጲክ ባደረገችውና ከ260 በላይ ሰዎች በተሳተፉበት ፖል በ2024 ምርጫ ትልቁ የመምረጫ መስፈርታቸው የኢኮኖሚና የኑሮ ውድነቱ እንደሆነ ጠቁመው የነበረ ሲሆን 20 ከመቶው የስደተኞች ጉዳይና ደቡባዊ ድንበር እንዲሁም 10 ከመቶው የጤና ተደራሽነትን በዋና ምክንያትነት አስቀምጠው ነበር። በዚህ ዙር ምዘናም 62% መራጮች የስደተኛ ፖሊሲንና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋነኛ መመዘኛቸው እንደሆነ አስታውቀዋል።
በዚህ ፖል ከተሳተፉት 65% የሜሪላንድ ነዋሪዎች ሲሆኑ 18% ከዲሲ እንዲሁም 16% ከቨርጂንያ ተሳትፈውበታል።