የስሚዞንያን ናሽናል ዙ ባሳለፍነው ሳምንት ካማላ ተብላ የምትጠራውንና በዕድሜ የገፋችውና ተወዳጇን የእስያ ዝሆን ማረፍ በማስመልከት እጅጉን አንዳዘኑ አሳውቀዋል። ለአስር አመት ያህል የመካነ አራዊቱ ባለሞያዎች ሲንከባከቧት የቆዩ ቢሆንም ያደረባት የመገጣጠሚያ በሽታ መዳን ባለመቻሉና በሽታው ከሚያደርስባት ከፍተኛ ስቃይ እንድታርፍ ሲባል ባሳለፍነው አርብ ኖቨምበር 1 2024 በመካነ አራዊቱ ባለሞያዎች የምህረት ግድያ (euthanasia) ተደርጎላታል።
ካማላ ዕድሜዋ 50 ዓመት ገደማ እንደሆነና ይህ ዕድሜ ለዝሆኖች አማካይ እንደሆነም ተነግሯል። የመካነ አራዊቱ ሰራተኞች ካማላ ብልህና ተመእራማሪ እንደነበረች ይናገራሉ። እንዲሁም ከሌሎቹ ዝሆኖች በተለየ የመሪነት ባህርይን ታሳይ ነበር ብለዋል። ካማላ በግንቦት 2014 ለመጀምሪያ ጊዜ ወደ መካነ አራዊቱ ስትመጣ ጀምሮ መገጣጠሚያዎቿ ከተለመደው የተለዩ እንደነበሩና ይህም የሰውነቷን ቅርጽ የተለየ እንዲሆን እንዳደረገው ታይቶ እንደነበር ተገልጿል።
ይህ የምህረት ግድያ ሲከናወን ሌሎቹ ዝሆኖች በቦታው እንዳልነበሩ ሆኖም ካማላ ካረፈች በኋላ ግን መተው እንደተሰናበቷት መግለጫው አክሎ አብራርቷል። ካማላ በ1975 በስሪላንካ እንደተወለደችም ተነግሯል። በ13 የእስያ አገራት የሚገኙት የእስያ ዝሆኖች የመጥፋት አደጋ ከተጋረጠባቸው እንሣት ተርታ የሚመደቡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከ30ሺ እስከ 50ሺ ያህል ብቻ በአለም ላይ እንደቀሩም ባለሞያዎች ይተነብያሉ። ዜናውን ያገኘነው ከስሚዞንያን ናሽናል ዙ ድረ-ገጽ ነው።
የምህረት ግድያ እንስሳት በማይድን በሽታ ከተያዙና ስቃይ ካለባቸው ስቃዩን ለማቆም የሚደረግ ግድያ ነው::