ሰሞኑን በዲሲና አካባቢው ያሉ የድንገተኛ ህሙማን መቀበያ ክፍሎች በርካታ በሳምባ በሽታ በተያዙ ሰዎችን እያስተናገዱ እንደሆነ ሜድስታር አስታወቀ። በአካባቢያችን 33 የድንገተኛ ህሙማን ማስተናገጃዎች ያለው ሜድስታር እንዳስታወቀው ከሆነ በኦክቶበር ብቻ 1758 ሰዎች በሳምባ ህመም(ኒሞንያ) ተይዘው ህክምና እንደተደረገላቸውና ባለፈው አመት በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ቁጥር አንጻር የ358% ጭማሪ እንዳለው ተጠቁሟል። በ2023 ኦክቶበር ወር በተመሳሳይ ህመም ተጠቅተው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ቁጥር 391 ብቻ ነበር። ይህ የሳምባ ህመም በአብዛኛው ሰዎች ዘንድ ቀላል እንደሆነና በርካቶች ያለሌላ ሰው ድጋፍ ራሳቸውን ችለው ወደሆስፒታል ስለሚመጡ ዎኪንግ ኒሞንያ የተባለ ስም ተሰቶታል።
በዚህ ህመም በአብዛኛው እየተጠቁ ያሉት ታዳጊዎች እንደሆኑና አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ10-17 እንደሆኑ ተነግሯል። ዕድሜያቸው ከ0 እስከ 9 ባሉ ህጻናት ታማምሚዎች ቁጥርም ቀላል በማይባል ሁኔታ እንዳሻቀበ የሜድስታር ድንገተኛ ህክምና ተባባሪ ዳይሬክተር የሆኑት አማንዳ ጆይ ለ ደብሊው ቲ ኦ ፒ ተናግረዋል።
ኃላፊዋ እንዳሉት ህመሙ በዋናነት በትኩሳትና ከባድ ሳል የሚኖረው ሲሆን ለቀናትና ሳምንታት የሚዘልቅ አክታም እንደሚኖረው ተናግረዋል። አንዳንድ ታማሚዎች ላይ እንደ አስም ያለ ከበድ ያለ ምልክት እንደሚያሳይይም ከዛ ካለፈም የአዕምሮ ኢንፌክሽን ሊያመጣ እንደሚችል ባለሙያዋ ተናግረዋል።
ይህ ህመም በእርግጥ ታክሞ መዳን የሚችል ሲሆን ባለሞያዎች ግን ሰዎች ሳይታመሙ በፊት እጃቸውን በመታጠብና አስፈላጊ ሲሆን ማስክ በማድረግ በሽታውን ሳይዛቸው በፊት መከላከል እንደሚችሉ መክረዋል።