12/12/2024

ይህ በ2445 Lyttonsville Rd, Silver Spring, MD 20910 የሚገኝ አፓርትመንት መነሻው ባልታወቀ ፍንዳታ ከባድ የቃጠሎና የመደርመስ አደጋ ደርሶበታል። ከስር በምስሉ እንደሚታየው የህንፃው አንድ አካል እስኪቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የአደጋው ሰለባ ሆኗል።

ይህ ህንፃ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የሌሎች በርከት ያሉ አገራት ስደተኞች ይኖሩበታል።

የሞንጎምሪ የእሳት አደጋ መከላከያ የፍንዳታው መነሻ የጋዝ ሊክ እንደሆነ ከደቂቃዎች በፊት አሳውቋል።

https://twitter.com/amritsathi/status/1499443836019486720

የሞንጎምሪ የእሳት መከላከያ ቺፍ ስካት ጎልድስታይን እስካሁን ድረስ 10 ሰዎች በአደጋው ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል ብለዋል። ከነዚህም ውስጥ አምስቱ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የካውንቲው የእሳት አደጋ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የሆኑት ፒት ፒሪንጀር አደጋው የበርካታ ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ ሲሉ ገልፀውታል።

አደጋው ሳይስፋፋ በፊት የአካባቢው ነዋሪዎች ያልሰሙ ሰዎችን በር በማንኳኳት ትልቅ የጀግንንት ተግባር አሳይተዋል።

እሳቱን ለማጥፋት እስከ150 ባለሞያዎች ከ ሞንጎምሪ ካውንቲና ከዲሲ የእሳት መከላከያና ማጥፊያ ቢሮ ተሳትፈውበታል። የቀይ መስቀልም በቦታው በመገኝት ከቤታቸው ለተፈናቀሉ እርዳታ እያደረገ እንደሆነ ተገልጿል።
የእሳት አደጋ ባለሞያዎች ከ10፡30 ጀምሮ በቦታው የተገኙ ቢሆነም በአደጋው አስከፊነት ምክንያት የህንፃው አንድ አካል ሙሉ ለሙሉ ከመደርመስ ሊታደጉት አልቻሉም። እስካሁን ባለው ግምት ከእያንዳንዱ ህንፃ እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች ያለመጠለያ ሊቀሩ እንደሚችሉ ይገመታል። የበለጠ መረጃ ከቀኑ 3፡00 ሰዓት ላይ መግለጫ ይሰጣል።

ተጨማሪ መረጃ ከ3፡00 ፒኤም በኋላ፡

  • ምንም አይነት አዲስ ጉዳት የለም
  • የአደጋ ተከላካዮች በቀጣይ ስራቸው የህንፃውን የቆሙ ግድግዳዎች የበለጠ ጉዳት እንዳያደርሱ ያፈርሷቸዋል
  • ከ6ቱ ህንፃዎች 3ቱ ነዋሪዎችን ማስተናገድ አይችሉም
  • በርከት ያሉ ግን በትክክል ቁጥራቸው የማይታወቅ የህንፃው ነዋሪዎች እስካሁን አልተገኙም
  • ነዋሪዎችን ማስተናገድ በሚችሉት 3 ህንፃዎች ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ምሽቱን ወደየአፓርትመንታቸው የሚገቡ ሲሆን
  • መግባት የማይቻልባቸው አፓርትመንት የሚኖሩት ደግሞ ለጊዜው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቀስ እንዲያወጡ ይደረጋል
  • የፍንዳታው መንስኤን በተመለከተ በርከት ያሉ መላምቶች ቢኖሩም ባለስልጣናቱ ግን እስካሁን ግልፅ መረጃ አልሰጡም
  • ተጎጂዎችን ለመርዳት የገቢ ማሰባሰቢያ ገጽ ተዘጋጅቷል ይህን ሊንክ ተጭነው እንዳቅምዎ ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ

ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱን እናቀርባለን

About Author

ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት