
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሁም እንደ የአሸባሪ ጥቃት የመሳሰሉ ሰው ሰራሽ ጉዳቶች በተለያዩ አካባቢዎች እና ጊዚያት ይከሰታሉ። ይኸን ተከትሎም ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን መጠን ለመቀነስ እና ለመከላከል፤ ዜጎች ስለ አደጋ ዝግጁነት በቂ ግንዛቤ እንዲያዳብሩ እንዲሁም ለድንገተኛ አደጋ ዝግጁ የሆነ የመኖሪያ ቤት እና አካባቢ እንዲኖራቸው ይመከራል።
ድንገተኛ አደጋ የምንለው በጤንነት፣ በህይወት ወይም በንብረት ላይ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ነው። እንደ የእሳት አደጋ፣ ዝርፊያ፣ ወይም ከባድ የጤንነት ችግር (ለምሳሌ፣ አለመተንፈስ፣ ራስን መሳት፣ ወይም የማያቋርጥ ደም መድማት) ያለ የድንገተኛ አደጋ በሚኖር ጊዜ፣ ከማንኛውንም ስልክ ላይ ወደ 9-1-1 ይደውሉ። ምን አይነት የድንገተኛ አደጋ እንዳለ ይንገሩዋቸው። ለመደወል አያይዘግዩ፣ እንግሊዝኛ የማይናገሩ ቢሆንም እንኳን፣ ለእርስዎ የሚሆን እገዛን ማግኘት ይችላሉ። ከግላዊ ድንገተኛ አደጋዎች በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የሆኑ የድንገተኛ አደጋዎች በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ሊከሰት ይችላል።
በዋናነትም ለሁሉም ዜጎች የሶሻል ሴኩሪቲን ጨምሮ መረጃዎችን በቶሎ ይዞ ለመውጣት አንድ ቦታ ሰብስቦ ማስቀመጥ፣ የአደጋ ጊዜ ስልክ ቁጥሮች ማወቅና በአቅራቢያ በስልክ ላይም ሆነ በወረቀት አትሞ መያዝ፤ በአደጋ ጊዜ ቆም ብሎ ሁኔታዎችን በማጤን፤ እርምጃ መውሰድ እና እርዳታ መጠየቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ናቸው።
አንዳንዴ ጊዜ ከፍተኛ ሙቀት፣ በረዶ፣ ጎርፍ ወይም ንፋስ እና የመሳሰሉት የኃይል እና የመገናኛ አገልግሎቶችን ሊያበላሹ ይችላሉ። በእነዚህ ወቅቶች ምን መደረግ እንዳለት የሚያሳዩ የጥንቃቄ መረጃዎችን አስተዳደሮች ያወጣሉ። ህጻናትም በየጊዜው በት/ቤት እንዲማሩ ይደረጋል። ይሁን እንጂ ስደተኛ ቤተሰቦች ይኸን መሰል መረጃ ሲያገኙም ሆነ በቂ የሆነ ዝግጁነት ሲያደርጉ አይታዩም። ኢትዮጲክስ የስደተኞች ዳግም ሰፈራ ቢሮ የሰው ልጅ አገልግሎቶች ቢሮ የድንገተኛ አደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ እና የዲሲ መንግስት አስተዳደር ቢሮና ከሲዲሲ ያገኘነውን መረጃ እንዲህ አደራጅተነዋል።
የቤተሰብ የአደጋ ዝግጁነት ተግባራት በአራት ይከፈላሉ። እነሱም 1) መረጃ መሰብሰብ 2) የቤተሰብ ዕቅድ ማውጣት 3) ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ቁሶችን ማዘጋጀት 4) ባላችሁበት ማህበረሰብ ውስጥ ለአደጋ መዘጋጀት
1) መረጃ መሰብሰብ
ለማንኛውም አደጋ በሚታቅድበት ጊዜ መረጃ ማግኘት የመጀመሪያው ደረጃ ነው። እራስዎንና ቤተሰብዎን ለመከላከል ማወቅ ያለብዎት ነገር ይህ ነው፦
- ሊከሰቱ ለሚችሉ ስለተለያዩ ዓይነት አደጋዎች ለማወቅና እርስዎና ቤተሰብዎ ለያንዳንዱ አደጋ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ ለማወቅ ይህንን መመሪያ ይጠቀሙ።
- የአደጋ መልህክቶችን ለመቀበል ለዲ.ሲ. ተጠንቀቅ (Alert DC) ይመዝገቡ።
- እያንዳንዱ የቤተሰብዎ አባል በአደጋ ጊዜ እንዴት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ማወቃቸውን ያረጋግጡ።
- በስራ ቦታዎ ቀጣሪዎ የአደጋ ወቅት ዕቅድ እንዳላቸው ይጠይቁ። ዕቅዱ ካላቸው ቅጂውን ወስደው ይመልከቱ።
- የልጅዎ ት/ቤት ወይም የመዋዕለ ሕፃናት ማዕከል ያለውን የአደጋ ጊዜ ዕቅድ ይኑርዎ። እርሱን ይከልሱትና ከልጅዎ ጋር ይወያዩበት።
- መሠረታዊውን የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታንና (First Aid) እንዲሁም የልብና ሳምባ መቀስቀሻ (CPR) ትምህርት ይማሩ።ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የአሜሪካን ቀይ መስቀል ማህበር በ http://redcross.org ይጎብኙ።
ለአደጋ ጊዜ ስለ መዘጋጀትን በተመለከተ የሚከተሉትን ድረ ገጾች ይጎብኙ፦
- የዲ.ሲ ትክክለኛ የአደጋ መረጃ፦ http://alert.dc.gov
- ተጨማሪ መረጃ ከዲ.ሲ የአገር ውስጥ ደህንነትና የአደጋ አያያዝ ደረጃ፦ http://hsema.dc.gov
- የዲ.ሲ መልቀቂያ መረጃና ካርታዎች፦ http://ddot.dc.gov
- አሜሪካን የአገር ውስጥ ዳህንነት መረጃ፡ http://ready.gov
- ተጨማሪ መረጃ ከፌደራል መንግሥት፡ https://www.fema.gov/emergency-managers/individuals-communities/preparedness-activities-research-webinars
- የአሜሪካን ቀይ መስቀል ማህበር፡ http://redcross.org
2) የቤተሰብ ዕቅድ ማውጣት
ዝግጅት የሚጀምረው እቅድ ከማውጣት ነው። በአደጋ ጊዜ እርስዎና ቤተስብዎ ሁኔታዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ይችሉ ዘንድ ቀላል ዕቅድ ለማዘጋጀት ሊረዳዎት የሚችለውን ከዚህ በታች ያለውን ዝርዝር ይጠቀሙ፦
- ይህንን ዝርዝር መሠረት በማድረግ የቤተሰብ ስብሰባ አድርገው የአደጋ ዕቅድ ያውጡ።
- የቤትዎን የወለል ፕላን ስለው ከያንዳንዱ ክፍል መውጫ ሁለት በሮችን ምልክት ያድርጉ።
- የፍጆታ ዕቃዎችን(ውኃ፣ ጋዝ፣ ኮረንቲ)መቼና እንዴት ከዋናው ማጥፊያና ማብሪያ ጋር እንደሚያጠፉት ይወቁ።
- በእርስዎ በኩል ቤተሰቡ መልሶ የሚገናኝበትን ከእስቴት ውጭ ያለ ዘመድ ወይም ወዳጅ ይምረጡ።(በአደጋ ጊዜ የአካባቢ ስልክ መሥመር የተያዘ ቢሆን ከእስቴት ውጭ መደወል ይቀል ይሆናል)። የሰዎቹን ስም፣ ስልክ ቁጥር፣ እንዲሁም ኢ-ሜይል አድራሻ ለያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ይስጡ።
- ልጆች የረጅም ርቀት ስልክ እንዴት እንደሚደወልና በአደጋ ጊዜ ዕርዳታ ለማግኘት 911 እንዴት እንደሚደውሉ ያስተምሩአቸው። የአደጋ ግዜ ቁጥሮችን በሁሉም ስልኮች ውስጥ ያስገቡ(ፕሮግራም ያድርጉ)።
- ከአደጋ በኋላ ቤተሰብዎ ተመልሶ የሚገናኝበትን ሁለት ቦታዎች ይምረጡ፦ እቤትዎ አጠገብ ያለ ቦታና እንደ አጋጣሚ ከአደጋው በኋላ ወደ ቤት መመለስ ባይችሉ ከአውራጃው ውጭ ያለ ሥፍራ ይምረጡ። የሁለቱንም መገናኛ ሥፍራዎች አድራሻና ስልክ ቁጥር ሁሉም ሰው እንደሚያውቅ እርግጠኛ ይሁኑ።
- ከመኖሪያ ቤታችሁ ወይንም ከሰፈር ውስጥ ያሉትን ሁሉንም መውጫ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን ይወቁ እንዲሁም ይለማመዱ።
- ጠቃሚ የሆኑ የቤተሰብ መዛግብትን(የልደት ማረጋገጨዎች፣ የጤና ጥበቃ መዛግብት፣ ፓስፖርቶችን) እሳትና ውኃ በማይደርሰበት ማስቀመጫ ወይም በባንክ የደህንነት ማጠራቀሚያ ውስጥ ያስቀምጡ።
- ዕቅድዎን ከሁሉም የቤተሰብ አባላት ጋር ይለማመዱ።

ከጎረቤቶችዎ ጋር በቅድሚያ ማቀድ ሕይወትና ንብረት ለማዳን ይረዳል።
- አደጋ ከመከሰቱ በፊት፣ ዕርዳታ እስኪደርስ ድረስ እንዴት በጋራ መሥራት እንደምትችሉ ለመነጋገር ከጎረቤቶችዎ ጋር ተገናኙ።
- ለማህበረሰብዎ በአደጋ ጊዜ ዝግጅት ድርጊቶች ይሳተፉ።
- ጎረቤቶችዎን ይወቁ እንዲሁም አረጋዊያንንና አካል ጉዳተኛን እንዴት መርዳት እንደምትችሉ ያገናዝቡ።
3) ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ቁሶችን ማዘጋጀት
የአደጋ ጊዜ ዕቃዎችን በቅድሚያ ማዘጋጀት ሥፍራውን የምትለቁ ከሆነና ወደ መጠለያ የሚገቡ ከሆነ ውድ ጊዜ ሊያድን ይችላል። የሚከተሉትን ዕቃዎች በጠንካራ፣ ለመሸከም በሚቀለው ቦርሳ ወይም ጎማ ባለው ሻንጣ (ኬሪ-ኦን) ውስጥ ይክተቱ። ዕቃውን በቀላሉ በሚደረስበት ቦታ ያስቀምጡ።
- ቢያንስ ለሦስት ቀን የሚበቃ ውኃ(በሰው በቀን አንድጋሎን)። በታሸገ፣ በማይሰበሩ ዕቃዎች ውስጥ ያስቀምጡት።
- ከሦስት እስከ አምስት ቀናት የሚበቃ የማይበላሽ የታሸገ ምግብና የቆርቆሮ መክፈቻ።
- በባትሪ ወይም በእጅ በማዞር የሚሠራ ራዲዮ የብሄራዊ ሜትሮሎጂና ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት
- የእጅ መብራትና ትርፍ ባትሪዎች።
- ፊሽካ – እርዳታ ለመጥራት።
- የተበከለ አየር እንዳያስቸግር ማስክ
- ዳክት ቴፕ ፕላስተርና የመስኮት መሸፈና ፕላስቲክ (ቤት ቆዩ ከተባለ።
- ጓንት፤ የቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክና ገመድ።
- ፒንሳና የተለያዩ መፍቻዎች (ጋዝና ውኃ ቧንቧ መዝጋት ካለብዎት) ወይንም የስዊስ አርሚ የኪስ ቢላዋ።
- ሳሙናና ሳኒታይዘር
- የሽንትቤት ሶፍት
- ቤቢ ዋይፕ
- የጥርስ ሳሙናና ብሩሽ
- ያሉበት ስቴትና የጎረቤት ስቴቶች ማፕ
- ለእያንዳንዱ ሰው አንድ አንድ ተጨማሪ ልብስ
- ብርድ ልብስ ወይንም ያልጋ ልብስ
- የዝናብ ልብስ
- የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች
- በኃኪም የታዘዙ መድሃኔቶች ካሉ
- የጉንፋን መድሃኒቶች
- የአለርጂ መድሃኒቶች
- ክብሪት/ላይተር
- ወሳኝ ዶክመንቶች (ፓስፖርት፤ የልደት ሰርተፊኬት፤ የባንክ ወረቀት፤ የመሳሰሉ።
- ካሽ (ጥሬ ገንዘብ)
ከነዚህ በተጨማሪ ህጻናትና የቤት እንሥሳት ካሏችሁ ለነሱ የሚሆኑ ቁሶች ማሟላት ያስፈልጋል።
4) ባላችሁበት ማህበረሰብ ውስጥ ለአደጋ መዘጋጀት (ማጤን)
- በምሄዱበት ቦታ ሁሉ አካባቢዎን በማጤን እራስዎንና ቤተሰብዎን መርዳት ይችላሉ።
- ተጠርጣሪ ወይም ጠባቂ የሌላቸው ቦርሳዎችን ወይም የተለየ ፀባይ የሚያሳዩትን ሰዎች በዓይንዎ ይከታተሉ።
- ያልተለመደ ባህርይ፣ ተጠርጣሪ ወይም ጠባቂ የሌላቸውን እሽጎች፣ እንዲሁም ለየት ያሉ መሣሪያዎችን ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም ለዳህንነት ሠራተኞች ያመልክቱ።
- እሽጎችን ወይም ሌላ ዕቃዎችን ከማያውቁአቸው ሰዎች በጭራሽ አይቀበሉ።
- ደመነፍስዎትን ቢከብድዎት፤ ቢቀፍዎት፣ ወይም አንድ ነገር ስህተት ቢመስልዎ፣ አካባቢውን ለቀው ለመሄድ አይጠራጠሩ።
- ከሁሉ የሚቀርበው የአደጋ ጊዜ መውጫ የት እንዳለ ይወቁ።
ለተጨማሪ ዝርዝር መዘጋጃ ዶክመንት በሲዲሲ የተዘጋጀውን ዶክመንት ሊንኩን በመጫን ያግኙ።