Screenshot 2025-04-07 at 8.50.32 PM

አይስ (ICE) ወደ ኤልሳልቫዶር ዲፖርት ያደረገው የቬንዙዌላ ዜጋ ስደተኛ በስህተት እንደሆነና በአስተዳደራዊ ግድፈት ምክንያት ይህ ሊፈጠር እንደቻለ አስታውቆ ነበር። ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ የተባለ የ29 ዓመት ወጣት በስህተት በመንግስት አካላት ታስሮ ማርች 15 ወደ ኤልሳልቫዶር ከተላከ በሁዋላ በአስከፊው የማጎርያ ካምፕ እንደገባ ተነግሯል።


ይህንን ተከትሎም ወቀሳ የቀረበበት ዋይት ኃውስ በፕሬስ ሴክሬተሪ ካሮሊን ሌቪት በኩል “ይህ የተፈጠረው በአስተዳደራዊ ስህተት ነው። ይህም ቢሆን ግን የትራምፕ አስተዳደር ይህ ወደ ኤልሳልቫዶር ዲፖርት የተደረገ ግለሰብ የኤም ኤስ 13 የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል እንደሆነ በቂ መረጃ እንዳላቸውና በፍጹም ወደ አሜሪካ እንደማይመጣና አልፎ ተርፎም ይኸው ሰው በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ተሳትፎ እንደነበረው በቂ መረጃ አለን” ብለዋል።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ባለቤቱ ጄኒፈር እንደሚሉት “አይስ አብሬጎ ጋርሲያን ማርች 12 ኮሌጅ ፓርክ በሚገኘው አይኪያ መደብር አቅራቢያ ከልጁጋ ሌሎች ሁለት ልጆቹን ከትምህርት ቤት ሲመለሱ ለማምጣት እንደወጣ የያዙት ሲሆን ወደ መኪና ሲያስገቡት እኔን ወስደው እንድሰናበተው ነገሩኝ” ብላለች።


አብሬጎ ኮሌጅ ፓርክ አቅራቢያ ከታሰረ በኋላ ወደ ባልቲሞር ማቆያ ጣቢያ እንደሄደና ቀጥሎ ወደ ሉዊዚያናና፤ ቴክሳስ አድርጎ ኤልሳልቫዶር ወደሚገኘው ወደ ቼንትሮ ኮንፋይንመንቶ ደል ቴሮሪዝሞ ወደተባለው አስከፊ እስር ቤት ዲፖርት ተደርጓል።


የኪልማር አብሬጎ ባለቤት ጄኒፈር መጀመሪያ ወዴት እንደወሰዱት እንዳላወቀች ሆኖም በኤልሳልቫዶር ፕሬዘደንት ትዊተር ላይ የተለጠፈውንና አዲሶቹ እስረኞች ጸጉራቸውን ሲላጩና የሚያሳየውን ቪዲዮ ስታይ ከታሳሪዎቹ ውስጥ ባሏን ማግኘቷን ተናግራለች።

የኪልማር አብሬጎ ጠበቃ ሉቺያ ኪውሪዬል እንደሚሉት አብሬጎ በ2019 ዲፖርት እንዳይደረግ ከፍርድ ቤት መተማመኛ ወረቀት እንዳለውና ይህ ወረቀት ላይ ይህ ሰው አደገኛነቱ ካልተረጋገጠ ወደ ዲፖርቴሽን እንዳይሄድ የሚገድብ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ጠበቃዋ ጉዳዩን ግሪንቤልት ሜሪላንድ በሚገኘውና የዩ ኤስ ዲስትሪክት ዳኛ ፓውላ ዢኒስ በተሰየሙበት የፌደራል ፍርድ ቤት የወሰዱት ሲሆን አርብ ኤፕሪል 4 ዳኛዋ የፌደራል መንግስቱ ይህንን ሰው እስከ ሰኞ ኤፕሪል 7 ከኤልሳልቫዶር እንዲመልሰው አዘዋ።


በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ያሉት የመንግስት ጠበቆች ታዲያ ቅዳሜ ኤፕሪል 5 መልሳቸውን ይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በምላሻቸውም የዳኛው የፌደራል መንግስቱ ከሌላ ሉዓላዊ አገር መንግስትጋ ተደራድሮ አሸባሪዎችን እንዲመልስ የማዘዝ ስልጣን እንደሌለውና ህገ መንግስቱን የሚጻረር አካሄድ እንደሆነ አስረድተዋል። የመንግስት ጠበቆች አክለውም “ፍርድ ቤት የታገቱ ሰዎችን ከሀማስ አስለቅቁ ወይንም በዩክሬን ያለውን ጦርነት አስቁሙ ብሎ ቢፈርድ ራሱ የፌደራል መንግስቱ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያበቃ ሀይል የለውም” ብለዋል።

ዳኛውም የአብሬጎ ጠበቆች ለመንግስት ምላሽ እስከ ዕሁድ ከሰዓት እንዲያስገቡ አዘዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስትን ወክሎ ሲከራከር የነበረው ጠበቃ በአግባቡ መንግስትን አልተከላከለም በሚል ምክንያት ከቅዳሜ ኤፕሪል 5 ጀምሮ አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስድ ተደርጓል። የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ፓም ቦንዲ ዕሁድ ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይም መንግስትን ወክለው ክሱን ሲከላከሉ የነበሩት አቃቤ ህግ ሩቬኒ “የተከላካይ ጠበቃ በአግባቡ መንግስት መከላከል ባለመቻላቸው አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ ተደርጓል። ቀጥሎ የሚፈጠረውን አብረን የምናየው ይሆናል ብለዋል። ”

ዕሁድ በድጋሚ ጉዳዩን ለመስማት እንዲሁም የከሳሽን ምላሽ ለመስማት የተጠራው ችሎትም በድጋሚ መንግስት ኪልማር አብሬጎን እስከ ሰኞ ኤፕሪል 7 እኩለ ለሊት ካለበት እንዲመልስ ፈርደዋል።

ይህን ተከትሎም የመንግስት ጠበቆች ጉዳዩን በይግባኝ ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት (ሱፕሪም ኮርት)የወሰዱት ሲሆን ጉዳዩን እንዲያዩት የተመደቡት ቺፍ ጀስቲስ ጆን ሮበርትስ ጉዳዩን በደንብ ለማየት ጊዜ ስለሚያስፈልግ በማለት በመንግስት ላይ የተጣለውን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ለጊዜው እንዲቆም አዘዋል። ይህ ጉዳይ ውሳኔ እስኪያገኝም በስህተት ዲፖርት የተደረገው ኪልማር አብሬጎ ጋርሲያ በኤልሳልቫዶር እስር ቤት ይቆያል። በመጪዎቹ ቀናትም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ የፍርድ ውሳኔ በጊዜያዊነትም ቢሆን ለፌደራል መንግስቱ የመተንፈሻ ጊዜ ሰቶታል። በቀጣይ የሚሰየመው የሱፕሪም ኮርት ውሳኔት የሚሄድበት አቅጣጫና የህገመንግስት ትርጓሜ ታዲያ ለበርካታ ስደተኞች ወሳኝ ሁነት እንደሚሆን ይገመታል። ሱፕሪም ኮርት የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ካጸናና የፌደራል መንግስቱ ተበዳይን ከኤልሳልቫዶር እንዲመልሰው ካዘዘ የፌደራል መንግስት በስደተኞች ላይ የሚኖረውን ጫና እንዲቀንስና ፍርድ ቤቶች በስደተኞች ዲፖርቴሽን ጉዳይ ቁጥጥር ማድረግ እንዲችሉ የሚፈቅድ ውሳኔ ይሆናል። ይህም ስደተኞች የተሻለ መብት እንዲኖራቸውና በመንግስት የሚደርስባቸውን አላግባብ ከአገር መባረር (ዲፖርቴሽን) በፍርድ ቤት እንዲከራከሩ ዕድል ይሰጣቸዋል።


ያ ሳይሆን ቀርቶ ሱፕሪም ኮርት ለፌደራል መንግስት ከፈረደ ኪልማር በዛው እንደታሰረ ከመቅረቱ በተጨማሪ አንድ ሰው አንዴ ዲፖርት ከተደረገ በኋላ የፌደራሉ ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ምንም ማለት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል የሚል የህግ ትንታኔ ተግባራዊ ይሆናል። ይህም አንድ ሰው ዲፖርት ከተደረገ በኋላ በፍርድ ቤት ፍትህ ስለማያገኝ የፌደራል ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ሰዎችን ያለአግባብ ዲፖርት እንዲያደርጉ በር ሊከፍት ይችላል። ስደተኞችም ዲፖርት ከመደረጋቸው በፊት ጉዳያቸውን እንዲከራከሩ ያስገድዳል።

About Author

Subscribe - የኢትዮጲክ ልዩ መረጃዎች፤ የዲ ኤም ቪ ዜናዎች በአማርና በኢሜይልዎና በስልክዎ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ

* indicates required
ይህን መረጃ ለወዳጅ ዘመዶችዎ ሼር ያርጉት

Sign In

Register

Reset Password

Please enter your username or email address, you will receive a link to create a new password via email.