
ፕሬዘደንት ትራምፕ ዛሬ ረቡዕ ባወቱት አዋጅ በአስራ ሁለት አገራት ያሉ ሰዎች ለአገር ደህንነት ስጋት ናቸው በሚል ምክንያት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ አግደዋል። በዚህ ዕግድ ውስጥም ኤርትራን ጨምሮ አፍጋኒስታን፤ በርማ፤ ቻድ፤ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፤ ኢኳቶሪያል ጊኒ፤ ሄይቲ፤ ኢራን፤ ሊቢያ፤ ሶማሊያ፤ ሱዳን እና የመን ተካተዋል። ሙሉ ለሙሉ ከታገዱት አገራት በተጨማሪም እንደ ብሩንዲ፤ ኩባ፤ ላኦስ፤ ሴራሊዮን፤ ቶጎ፤ ቱርክሚኒስታንና ቬንዙዌላ ያሉት ደሞ በከፊል ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።
የትራምፕ ዋይት ኃውስ ለዚህ ክልከላ መንስዔ ነው ያለው ከሰሞኑ በኮሎራዶ በአንድ ግብጻዊ አማካኝነት የደረሰውን የሽብር ተግባር እንደሆነ ቢጠቅስም ግብጽ ግን በዚህ ክልከላ አልተካተተችም። ይልቅስ ፕሬዘደንት ትራምፕ የግብጽን ሁኔታ እያጤኑት እንደሆነ አስታውቀዋል።
በዚህ አዋጅ ላይ በሴክሽን 2 ላይ በዝርዝር ከተቀመጡት አገራት ተርታ ባለችው ኤርትራ ስር አገሪቱ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተካተተችበትን ምክንያት ሲያስቀምጥም “ዩናይትድ ስቴትስ የኤርትራ ማዕከላዊ ባለስልጣን ለዜጎቹ ፓስፖርትና ሌሎች መረጃዎችን የመስጠት ብቃት እንደሚጠራጠርና በተጨማሪም የዜጎቹን የወንጀል ሬከርዶችን በአግባቡ ለዩናይትድ ስቴትስ እንደማያጋራ የተጠቀሰ ሲሆን በተጨማሪም ከአሜሪካ ዲፖርት የሚደረጉ ዜጎችን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ እንደ አንድ ምክንያት ተቀምጧል።
በተጨማሪም የኤርትራውያን በቢ1ናቢ2 ቪዛ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ የሚቆዩ ዜጎቿ 20.09% በመሆኑ እንዲሁም በF, Mና J ቪዛ የገቡ ዜጎቿ ደሞ ከ55.43% በላይ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ እንደሚቆዩ አስታውቀው በማንኛውም የቪዛ አይነት ሙሉ ለሙሉ እንዳይገቡ ተደንግጓል።
ይህ ክልከላ ወደስራ ከመግባቱ በፊት ቪዛ የተፈቀደላቸውን ሰዎች አይመለከትም።