
ኢትዮጲክ – እንግዳችን ስለሆነሽ እናመሰግናለን። እስቲ ያለሽበትን የሙያ ዘርፍ እና ማንነትሽን አስተዋውቂን።
ነጻነት – እሺ እኔም በጣም አመሰግናለሁ። ነጻነት ቦጋለ እባላለሁ። የቢዝነስ ማኔጅመንት ባለሞያ ነኝ። በኮርፖሬት ዓለም ላይ ነው እየሰራሁ ያለሁት። ከ18 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ አለኝ። አሁንም ይሄንኑ ነው በመሥራት ላይ ያለሁት። በተጨማሪም ደግሞ የልዩ ኤቨንትስ አጋር መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ነኝ።
ኢትዮጲክ – እስቲ የልዩ ኤቨንትስ የመጨረሻ መርኃ-ግብር ምን ይመስል ነበር አጠር አድርገሽለአንባቢዎቻችን አጋሪልን?

ነጻነት – ልዩ ነበረ! (በአድናቆት)… ያው እንደተለመደው ዝግጅቱ የተካሄደው በወሩ መጨረሻ አርብ ላይ፤ ሜይ 30 (እ.ኤ.አ) ነበር። ልክ እንደስማችን ልዩ ነበረ ማለት እችላለሁ። ከሁሉም ሙያ እና እውቀት ዘርፍ የተውጣጡ ሰዎች ነበሩ፣ እዚህ ሀገር ተወልደው ያደጉም፣ እዚህ ሀገር መኖር ከጀምሩም 40 ዓመት የሆናቸውም፤ እንዲሁም ደግሞ ገና ወደዚህ ሀገር ከመጡ ሁለት ወር ብቻ የሆናቸው ሰዎች ሁሉ ተሳትፈውበታል። ከሙያ አንጻር ካየነው ደግሞ ከህግ ባለሞያ፣ እዚህ ሀገር በነጻ የትምህርት ዕድል የመጡ ተማሪዎች፣ ስራ ፈላጊዎች፣ የሪል ስቴት ኤጀንቶች፣ ጸሀፊዎች፣ በጎ አድራጎት መስራቾች፣ የአርት ባለሞያዎች ሁሉ ነበሩበት። እናም በጣም ውጤታማ ነበረ። ኢትዮጲክስም አንዷ እንግዳችን ስለነበረች ደግሞ እናመሰግናለን። በጣም ውጤታማ የነበሩ ሰዎች ህብረት የመሰረቱበት፣ አብሮ ስለመስራት፣ ሀሳብ ስለመቀያየር በጎ ፈቃደኞችን ስለማግኘት ውይይት የተደረገበት እጅግ አስደሳች መርሃ ግብር ነበረ። ሁልጊዜም እንደምናስበው ቀጣይነት ያለው ግንኙነት እንዲፈጠር ነው የምንፈልገው። እድገት እና አብሮ መሥራት እንዲኖር ነው ዋናው ዓላማ። ይሄንን ያሳካ በጣም የሚያጓጓ ኢቨንት ነው የነበረው።
ኢትዮጲክ – መርሃግብሩ ሲዘጋጅ ምን ዓይነት ይዘት አለው?
ነጻነት – መርሃ ግብራችን ከማታ 6- 9 ፒ.ኤም ነው። ሁሌም ስድስት ሰዓት ላይ በር እንከፍት እና ለ30 ደቂቃ ያክል ቅድመ ኔትወርክ እናደርጋለን። ከዛ በኋላ እንግዲህ መርሃ ግብሩ ተጀምሮ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያክል የተለያዩ ሰዎች እራሳቸውን፣ ተቋማቸውን አሊያም ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት ዝግጅት ይካሄዳል። ከዛ በመቀጠል ደግሞ ሁሉም ሰው ከሚፈልገው ሰው ጋር ተገናኝቶ እና ተዋውቆ ኔትወርክ የሚያደርግበት ሰፋ ያለ ሰዓት ይኖረናል ማለት ነው። ይሄንን አካሄድ ይዞ ነው መርሃግብሩ የሚካሄደው።

ኢትዮጲክ – ልዩ ኤቨንትስ መቼ እና እንዴት ተመሰረተ? ምን ነበር መነሻው?
ነጻነት – እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ኮርፖሬት ዓለም ውስጥ ነበር የነበርኩት። በተለይ ደግሞ በባንኪንግ ኢንደስትሪ ውስጥ ነበር የምሰራው። ያኔ የተለያዩ ኢቬንቶችን እናዘጋጅ ነበር። በተለይም ለኢንቨስተሮች እና ለባለሃብቶች የሚሆኑ መርሃ ግብሮችን ነበር የምንዘጋጀው። እና በዛን ወቅት ይሳተፉ የነበሩ ሰዎች ላይ የማየው ነገር ሰዎች ተገናኝተው ሃሳብ ሲቀያየሩ የሚኖራቸው ስሜት መዝናኛ ስፍራ ከመሄድ ያለፈ ነበር። እዚህ ሀገር ስመጣ ደግሞ ብዙ ሰዎች በዕለት ተዕለት ጉዳዮች ተይዘው ሁል ጊዜ ይሯሯጣሉ። እንጂ ቆም ብለው ምን አዲስ ነገር አለ? ሰዎች ምን እያደረጉ ነው ብለው አያዩም። ፕሮፌሽናል ኔትወርካቸውም አብዛኛውን ጊዜም ጠበብ ያለ ነው። ስለዚህ እስቲ መድረኩ ይፈጠር እና ሰዎች በየጊዜው እየመጡ ሀሳባቸውን ይቀያየሩ አዳዲስ ሃሳቦችን እያመጡ ሌላም ሀሳብ የሚያፈልቁበት መድረክ ይኑር በሚል ነው ልዩ ኤቨንትስ የተመሰረተው።
ኢትዮጲክ – መርሃግብሩ ምላሽ ምን ይመስላል? ከተጀመረ በኋላ በምን መልኩ እያደገ ነው?
ነጻነት – ከተጀመረ እንግዲህ አንድ ዓመት ከሁለት ወር አካባቢ ሆኖታል። ስንጀምር አጀማመራችን ለኮርፖሬቶች እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ነበረ። አሁን ግን ይበልጡን ሰው እያወቀው እና እየወደደው የመጣው በተለይም ኔት ወርኪንግ ኢቨንታችንን ነው። እና የሰዉ ምላሽ እጅግ አስደሳች ነው። መርሃግብሩ ከወር ወር ድረስ ሰዎች እየቸኮሉ የሚመጡበት ሆኗል። እንደውም በሌሎች ስቴቶች ያሉ ሰዎችም ጋር እውቅና አግኝቶ፤ ወደዚህ ሲመጡ የእኛ መርሃግብር ላይም ለመገኘት እንዲመቻቸው አድርገው አቅደው ይመጣሉ። ባለፈው ወር ለምሳሌ ከአትላንታ እና ከሚኒሶታ እንግዶች ነበሩን። በዚህ ወር ደግሞ ከቴክሳስ እና ከቦስተን እንግዶች ነበሩን። እንግዲህ እያደግን እና ተወዳጅነት እያተረፍን ነው የመጣነው።

ኢትዮጲክ – ከዚህ ዝግጅት በተጨማሪ ልዩ ኢቨንት ተቋም የሚሰራቸው ሌሎች ሥራዎች ምንድናቸው?
ነጻነት – የመጽሀፍት ምርቃቶችን እንሰራለን። የተያዩ ዕድሎች ሲመጡም ለሌሎች ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለእኛ ለልዩ ኤቨንትስም ዕድሎች ናቸው። ስለዚህ ጸሃፊዎች መጽሃፍ ማስመረቅ ሲፈልጉ ኔትወርካችንን ተጠቅመን እናዘጋጃለን። እንግዲህ ኤቨንት ማቀድ እና መተግበር በራሱ ሳይንስ ነው። በጀቱን አካባቢውን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን በሙሉ አስቀድሞ ማቀድ ይፈልጋል። በተጨማሪ ደግሞ ስብሰባዎችን እና ኮንፈረንሶችንም ለተቋማት እና ለማኅበራት እናዘጋጃለን። የንግድ ዝግጅቶችንም እናዘጋጃለን። እንግዲ ኮርፖሬት ኢቨንቶችን እናዘጋጃለን ስንልም ስብሰባዎችን እና ኮንፈረንሶችንም ማለታችን ነው።
ኢትዮጲክ – የወደፊት ዓላማችሁስ ምን ይመስላል?
ነጻነት – ተቋማችን ገና ዳዴ እያለ ነው። ብዙም ጊዜ አልሆነው። ነገር ግን የሀበሻ ቴድ ኤክስ ወይም ቴድ ቶክ መሆን ነው የምንፈልገው። ሰዎች እንዲረዱት የምንፈልገው ሀሳብ ምንድነው? እኛ ላማንኛውም ሰው ማይካችን ክፍት መሆኑን ነው። የግድ ንግድ ውስጥ ብቻ ያለ ሰው መሆን የለበትም። እኔ ለሰዎች ሃሳቤን ማጋራት እፈልጋለሁ አሊያም ከሌሎች መስማት እፈልጋለሁ የሚል ሰው በሙሉ የሚካፈልበት እንዲሆን ነው የምሰራው። ከንግድ ውጭ በተላያዩ ሙያዎች ላይ ሰዎች ተመራማሪዎች ስለ ሥራቸው ስለጥናታቸው የሚያቀርቡበት መድረክ እንዲሆን እንሻለን። ስዎች በእኛ መድረክ ላይ በራስ መተማመናቸውን እንዲያዳብሩ እንፈልጋለን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ፕሮፌሽናል የሚለው ቃል ይከብዳቸውን ይቀራሉ። ነገር ግን የእኛ መድረክ ምንም የተለየ ዘርፍ ላይ ያተኮረ አለመሆኑን መናገር እፈልጋለሁ። ዋናው ነገር አብረን ማደግ እንችላለን የሚለው ነው።
ኢትዮጲክ – እስቲ አሁን ደግሞ ጥቂት ስለ ግል ህይወትሽ ንገሪን።
ነጻነት – ባለትዳር እና የአንድ ወንድ ልጅ እናት ነኝ። በአጠቃላይ በትዳር ውስጥ 23 ዓመታት ሆኖኟል። እዚህ ሀገር ከመጣሁ ደግሞ ዘጠኝ ዓመቴ ነው። በሙያዬ ብዙ ነገሮች ውስጥ አለሁ። ክፍተቶችንም ስላየሁ ነው ይሄንን መርሃግብር ልንፈጥር የቻልነው። ወደ ግል ህይወትሽ እያልከኝ እንግዲህ ወደ ልዩ ኤቨንትስ መጥቻለሁ። ልዩን በጣም ሰለምወዳት ነው። ከጓደኛዬ ከሩት ሲሳይ ጋር ነው የመሰረትነው። በሥራችን በጣም ደስተኞች ነን። ሁለታችንም ከስራችን ባሻገር ነው ይሄንን እየሰራን ያለነው። የቤተሰብ ጉዳዮችም አሉብን። ነገር ግን ሰዎች መጥተው ተደስተው እና አትርፈው ሲሄዱ ላይክ ማይንድድ የሆኑ (ተመሳሳይ አመለካከት እና ፍላጎት) ያላቸው ሰዎች መገናኘት እንግዲህ ከመዝናናትም በላይ ነው።
ኢትዮጲክ – ቀጣይ የልዩ የኔወርኪንግ ዝግጅታችሁ መቼ ነው? ለመታደም የሚሹ ሰዎችስ ምን ያድርግ?
ነጻነት – ቀጣዩ የሰኔ ወር ዝግጅታችን በመጨረሻው አርብ ጁን 27 (እ.ኤ.አ) ነው የሚሆነው ስድስት ሰዓት ላይ ይጀምራል። ዝግጅቱ የሚካሄደው በሲልቨር ስፕሪንግ ጆሪጂያ አቬኑ 8070 ነው። በዚህ ደግሞ ለሚተባበረን አሻጋሪ ኮንሰልታንሲ እናመሰግናለን። ዝግጅቱን ለመታደም ሰዎች አስቀድመው በተለያዩ መተግበሪያዎች ላይ መመዝገብ አለባቸው። በእርግጥ በዕለቱም በር ላይ መመዝገብ ይችላሉ። ነገር ግን ለእኛ ለዕቅድ ምን ያክል ሰው እንደሚመጣ ለመበጀት እንዲመቸን አስቀድመው ቢመዘገቡ መልካም ነው። በተለይ ንግግር አቅራቢ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች አስቀድመው ካልተመዘገቡ አይሆነም። ምክንያቱም በአንድ ዝግጅት ላይ የሃሳብ መደጋገም እንዲኖር አንፈልግም። ሁለት የቴክኖሎጂ ባለሞያዎች ቢኖሩ በአንድ ቀን መሆን አይቻልም ማለት ነው። ስለዚህ ቀድሞ የመጣ ይሰተናገድ እና የዘገየ በቀጣይ ወር ይሆናል። ንግግር እናቀርባለን የሚሉ ሰዎች አስቀድመው ርዕሴ አሊያም ይዤ የምቀርበው ምርት ይሄ ነው ቢሉን አስቀድሞ ለመዘጋጀት ይጠቅመናል።
ኢትዮጲክ – የልዩ ኤቨንትስ መስራች እና አጋር ሥራ አስኪያጅ ነጻነት ቦጋለ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
ነጻነት – እኔም አክብራቹ ስለጠራችሁኝ አመሰግናለሁ።