
ከዚህ ቀደም በኢትዮጲክ እንደተዘገበው የፌርፋክስ ካውንቲ ፖሊስ ከዚህ ቀደም ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽሟል ያሉትን ጊግሳ በቀለን ኦክቶበር 25 2023 በቁጥጥር ስር አውለውት የነበረ ሲሆን ተጠርጣሪው ከእስር ተለቆ ከሰሞኑ በሌላ ወንጀል ተጠርጥሮ በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ፖሊስ ዛሬ ሜይ 30 እንዳስታወቀው ጊግሳ በቀለ ከትላንት በስትያ ከሰዓት 5፡04pm ላይ በ11700 Fair Lakes አቅራቢያ የወሲባዊ ትንኮሳ ጥሪ እንደደረሳቸውና ሁለት ተጎጂዎች ለፖሊስ እንዳመለከቱ አስታውቀው ፖሊሶች አካባቢው ላይ ፍለጋ በሚያደርጉበት ወቅት 5:17 pm ላይ ሌላ ተመሳሳይ የስልክ ውንጀላ ከ13000 Fair Lakes ይደርሳቸዋል።
በዚህ የስልክ ጥሪ ላይ ደግሞ ተጠርጣሪው በመኪናው ውስጥ ሆኖ ግለ-ወሲብ (ሴጋ) ሲፈጽም እንደነበር የተነገራቸው ሲሆን ፖሊሶች ወደ ፌርሌክስ የገበያ ማዕከል ሲያቀኑ ግን ተጠርጣሪው ቀድሞ ተሰውሯል።
ፖሊሶች በአካባቢው ያሉ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎችን ሲመረምሩ ተጠርጣሪውን ከነመኪናው በቪድዮ ይታይ እንደነበር ይኸው የፖሊስ መግለጫ ያሳያል።
ይህ ሁሉ ሆኖም በተጨማሪ ማምሻውን 7፡41 ላይ አንድ ሌላ ተጨማሪ የወሲባዊ ትንኮሳ ከ 12200 Fairfax Towne Center ይደርሳቸዋል፤ ተጎጂዋም ለፖሊሶች በሰጠችው ቃል ተጠርጣሪው በመኪና ማቆሚያው አካባቢ እንደተጠጋትና ወሢባዊ ትንኮሳ እንዳደረሰባት ተናግራለች።
በመጨረሻም ፖሊሶች ምሽት 8፡12 ላይ ተጠርጣሪውን በመኖሪያ ቤቱ ለመያዝ ሲሄዱ ጥቃት እንዳደረሰባቸውና ይህ ተጠርጣሪም የ33 አመቱ ጊግሳ በቀለ በንጌሳ እንደሆነ ፖሊስ በመግለጫው አስታውቋል።
ጊግሳ ወደ ፌርፋክስ ካውንቲ ማረሚያ ቤት እንደተወሰደና በ2 ወሲባዊ ትንኮሳ ወንጀሎችና፤ አላግባብ ያልተሸፈነ ገላን በማሳየት፤ ለህግ አልገዛም በማለትና በሁለት የህግ አስገባሪ ላይ ጥቃት በመሰንዘር ወንጀል እንደተከሰሰና ያለ ዋስትና እንደታሰረ ፖሊስ አስታውቋል።