
ከ2019 ጀምሮ በዋሽንግተን ዲሲ ባለስልጣናት ተፈርሞበትና ህግ ሆኖ የጸደቀው የዲሲ ፖሊሶች የስደተኞችን ለፌደራል መንግስት እንዳይሰጡ የሚከለክለውን ህግ የሚሽር አዲስ ረቂቅ ህግ በዲሲ ከንቲባ ተዘጋጅቶ ለዲሲ ካውንስል አባላት ቀረበ። ይህም ረቂቅ ህግ በካውንስል አባላቱና በሌሎች የዲሲ ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ውዝግብን እንዳስነሳ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበውታል።
በ2019 የወጣው ህግ የፍርድ ቤት ማዘዣ ከሌለ በስተቀር የዲሲ ፖሊሶችና የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በቁጥጥራቸው ስር የሚገኙ ሰዎችን የስደተኛነት ደረጃ (ስታተስ) ለፌደራል መንግስት አሳልፈው እንዳይሰጡ ይከለክላል። ከንቲባ ሚውሪየል ባውዘር አሁን ይዘውት የመጡት ረቂቅ ደሞ ይህን ህግ ሙሉ ለሙሉ የሚሽር ሲሆን የከተማዋ ህግ አስከባሪ ፖሊሶችና ሰራተኞች ከአይስጋ በቅርበት እንዲሰሩ ያዛል። ከንቲባዋ ይህን እንዲያደርጉ ምክንያት ናቸው የተባሉት ደሞ የፕሬዘደንት ትራምፕ ጫናና የኮንግረስ የ1 ቢልየን ዶላር የበጀት ቅነሳ እንደሆነ ተነግሯል።
ከአምስት አመታት በፊት ከንቲባ ባውዘር ዲሲ ለስደተኞች የምትመች ከተማ ነች ሲሉ ተናግረው የነበረ ሲሆን ፕሬዘደንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ ግን በርካታ ለስደተኞች ይደረጉ የነበሩ ድጋፎችን ሰርዘዋል። ከነዚህም ውስጥ አንዱና ዋነኛው በከተማው የመንግስት ድረ ገጽ ላይ የነበረውንና ለስደተኞች መረጃ ይሰራጭበት የነበረውን ገጽ ማጥፋት አንዱ ነው።
ይዚህ ረቂቅ ደጋፊዎች ከንቲባዋ የፌደራል መንግስትን ትዕዛዛት ካላከበሩ ለከተማዋ የሚመደበው በጀት እንደሚቀንስና ይህ ከተማዋን ለማስተዳደር አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይከራከራሉ። በርካታ የከተማው ነዋሪ የሆኑ የፌደራል መንግስት ሰራተኞች ከስራ መቀነሳቸውን ጨምሮ ይህ አይነት የፌደራል መንግስ እርምጃዎች ከተማዋን አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚያስገባትም ይናገራሉ።
የዚህ ረቂቅ ተቃዋሚዎች ደሞ በበኩላቸው ስደተኞች የፌደራል መንግስት እርምጃን በመፍራት ወደ ፖሊስ እንዳይደውሉ እንደሚያደርጋቸውና ለጥቃት እንደሚጋለጡ እንደሚፈሩ ይናገራሉ። ከከንቲባዋ ውሳኔጋ እንደማይስማሙ ካስታወቁት አንዷና ዋነኛዋ በኮንግረስ የዲሲ ተወካይ ኤሌኖር ሆምስ ኖርተን ሲሆኑ ይህ እርምጃቸው ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እንዳልሆነና የዲሲን የራስን እድል የመወሰን ሂደት የሚሸረሽር ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የዲሲ ዋርድ 4 ካውንስል አባል የሆኑት ጃኒስ ሊዊስ ጆርጅ በበኩላቸው ላለፉት 5 አመታት የዲሲ ህግ ለከተማችን ስደተኞች ጥበቃ ሲያደርግ እንደቆየና ይህም ሰዎች ምንም አይነት የስደተኝነት ደረጃ ላይ ቢሆኑ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ሲያደርግ እንደቆየ ተናግረው በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስደተኛ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች ሰዎችን ከስራ ቦታና ከመንገድ እያፈሱ ሲወስዱ ቢያንስ ዲሲ የህግ ከለላ እንደነበራቸው አውስተው ምንም እንኳ ከንቲባዋ ከፌደራል መንግስትጋ ለመስራት ቢስማሙም እሳቸው ግን በፍጹም ለፌደራል መንግስት እንደማያጎበድዱ በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
የ2026 ረቂቅ ህግ የወደፊቷን የዲሲን መልክ የሚቀይረው ሲሆን የከንቲባዋ ኃሳብ ከተሳካ ዲሲ ወረቀት ለሌላቸው ወይንም ጉዳያቸው ላላለቀ ስደተኞች የማትሆን ከተማ ትሆናለች፤ ከተማዋ ለዘመናት የነበረው የማህበረሰብ ዕምነትና ተስፋም እንደሚሸረሸር ይጠበቃል። ይህ ህግ ሳይጸድቅ ከቀረ ደግሞ የፌደራል መንግስት ጫና ከተማዋ ላይ በተለይም በበጀት ቁጥጥር ከባድ እንደሚሆን ይጠበቃል።