
በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ላሉ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሰዎች በየአመቱ የሚሰጠውና ታዋቂው የሶሳይቲ ኦፍ ፕሮፌሽናል ጆርናሊስትስ የዲሲ ቻፕተር የዴትላየን ሽልማት ፕሮግራም በዘንድሮ ውድድሩ ኢትዮጲክና the 51st በጋራ ለስደተኞች ያጠናቀሩትን መጣጥፍ በOnline፣Non-Breaking News ዘርፍ ከመጨረሻ ዙር ተወዳዳሪዎች ተርታ (Finalist) መድቦታል።

የውድድሩ አሸናፊም በመጪው ማክሰኞች ጁን 10 2025 በናሽናል ፕሬስ ክለብ በሚኖረው የእራት ግብዣ ፕሮግራም ላይ ይፋ ይሆናል። በዘንድሮው የሲ ፒ ጄ ሽልማት ፕሮግራም ላይ በክብር እንግዳነተና በሆል ኦፍ ፌምነት በማህበሩ ዕውቅና የሚሰጣቸው ሰዎች የቪ ኦ ኤ ዳይሬክተር የሆኑት ማይክል አብራሞዊትዝ፤ ሪቻርድ ፕሪንስ፤ ታዋቂዋ የዲሲ ጋዜጠኛና የዋሽንግተን ኢንፎርመር ባለቤት ዴኒስ ሮላርክ ባርንስ ይገኙበታል።

ይህ መጣጥፍ በ the 51st “Worried about your immigration status amid Trump’s ‘mass deportation’ agenda?” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን በአማርኛ ደሞ “በርካታ ስደተኞችን አባርራለሁ” የሚለው የትራምፕ አጀንዳ አስጨንቆታል?” በሚል ርዕስ በኢትዮጲክም በ the 51stም ወጥቶ ለንባብ ቀርቧል።
ለዚህ መጣጥፍ መነሻ የነበረው የፕሬዘደንት ትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ኢትዮጲክ ለአንባቢዎቿ ባደረገችው መጠይቅ በተሰበሰበ የህዝብ ሀሳብ በርካቶች በእርግጥም መጨነቃቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጲክ መስራች ሔኖክ መንግስቱ በዚሁ መጠይቅ በመነሳት በወቅቱ ከህግ ባለሞያዎችጋ ዌቢናር በማዘጋጀት ሰዎች ጥያቄያቸውን በቀጥታ እንዲጠይቁና ምላሽ እንዲያገኙ ተሰርቶ ነበር።
የኢትዮጲክ ባልደረቦች በተለይም ይህ ስራ ከሀሳብ ወደ ተግባር እንዲቀየር ኃላፊነቱን ወስዶ ያገዘንንና እኛ ሳናውቀው ለዚህ ሽልማት በዕጩነት ስማችንን ለአዘጋጆቹ ያስተላለፈልንን የthe 51st ባልደረባ ኤሪክ ፋልኬሮን አብዝተን ለማመስገን እንወዳለን። ለመጣጥፉ መሳካት ከሁሉም አቅጣጫ የተረባረቡትን የ the51st ባልደረቦችን በሙሉ እንዲሁ ለማመስገን እንወዳለን።
ከሁሉም በላይ ደሞ ለምንልከው መጠይቅ ምላሽ ለምትሰጡን፤ ስንሳሳት ለምታርሙን፤ ከስር ከስር ጎበዞች ይህን አስተካክሉ፤ ይህን ጨምሩ ለምትሉን ለአንባቢዎቻችን እናንተን ማገልገል በራሱ ሽልማት ነውና ምስጋናችን የላቀ ነው።
በዚህ አጋጣሚ የህይወት ሁኔታችሁ የሚፈቅድላችሁና ጊዜው ያላችሁ አንባቢዎቻችን ቅዳሜ ሜይ 31 2025 10፡00am ላይ ባዘጋጀነው የአካባቢ ማጽዳት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመገኘት በማደጎ የወሰድነውን የሲልቨር ስፕሪንግ አቬኑ በማጽዳት አብራችሁን እንድታሳልፉ እንጋብዛችኋለን። ቦታው 8181 Georgia Ave, Silver Spring MD 20910. በዚህ የበጎ ስራ የሚመጡ ሰዎችን ቁጥር ለማወቅ እንዲያግዘን እባክዎ ይህን ተጭነው ይመዝገቡ። እናመሰግናለን።
