
ዜናው የቢቢሲ ነው
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን ለመቀበል ዳተኛ በመሆኗ ምክንያት የደቡብ ሱዳን ፓስፖርት ለያዙ የተሰጠ ማንኛውም ቪዛ መሰረዙን አስታወቁ።
ሩቢዮ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ አገራቸው ማንኛውም የደቡብ ሱዳን ዜጋ ወደ አሜሪካ በየትኛውም መንገድ እንዳይገባ እንደምታግድ ተናግረዋል።
“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎቹን በወቅቱ ባለመቀበሉ” ለችግሩ ተጠያቂ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት አዲሱ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ የተነሳ ሕገወጥ ስደተኞችን “በጅምላ ከአገር” እያስወጡ ነው።
“የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት አሜሪካን መጠቀሚያ ማድረግ የሚያቆምበት ጊዜ አሁን ነው” ሲሉ ሩቢዮ አስጠንቅቀዋል።
“አሜሪካም ሆነች ሌሎች ከአገራቸው የሚያስወጧቸውን ሰዎች አገራት ወድያውኑ መቀበል ይኖርባቸዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተሰማው ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ እርስ በርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ነው።
አሜሪካ በቀጠናው ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የካቲት 29 2017 ዓ.ም. በደቡብ ሱዳን የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ያልሆኑ ዜጎቿ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ አዝዛ ነበር።
የትራምፕ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ ጊዜ ጀምሮ ከአሜሪካ በሚባረሩ ዜጎቻቸው ምክንያት ከመንግሥታት ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል።
በጥር ወር የኮሎምቢያው ፕሬዝዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቻቸውን የጫኑ ሁለት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች አገራቸው እንዳያርፉ ከልክለዋል።
ፔትሮ ትራምፕ በኮሎምቢያ ላይ ከበድ ያሉ ታሪፎችን እና ማዕቀቦችን ለመጣል ቃል ከገቡ በኋላ ውሳኔያቸውን አጥፈዋል።