
ዛሬ ሰኞ ኤፕሪል 14 በዋይት ሀውስ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የኤል ሳልቫዶር ፕሬዘደንት የሆኑት ናይብ ቡኬሌ በስህተት ከፕሪንስ ጆርጅ ካውንቲ ዲፖርት የተደረገውን ኪልማር አብሬጎን የሚመልሱበት ምንም ምክንያት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ሰዎችም ኪልማ አብሬጎ ጋርሲያ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት የኤም ኤስ 13 የተደራጀ የወንጀል ቡድን አባል እንደሆነ እንደተፈረደበትና ፕሬዘደንት ትራምፕ ደሞ የኤም ኤስ 13 ቡድንን በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ስለወሰኑ ይህ ግለሰብ ምንም አይነት የኢሚግሬሽን ጥቅማጥቅም ማግኘት እንደማይችል ተናግረዋል።
የኤል ሳልቫዶር ዜጋ በመሆኑ ምንም እንኳ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲመለስ ቢወስንም የኤል ሳልቫዶር መንግስት አልመልስም ካለ ምንም ማድረግ እንደማይችሉና የኤልሳልቫዶርን ሉዓላዊነት እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት ፓም ቦንዲ በበኩላቸው የኤልሳልቫዶር መንግስት ግለሰቡን መልቀቅ ከፈለገ እኛ ሁኔታውን እናመቻቻለን፤ መመለሻ አውሮፕላንም እናዘጋጃለን ብለዋል።
የኪልማር አብሬጎ ጠበቃ በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር ደንበኛቸው የኤም ኤስ 13 ቡድን አባል እንደነበር ምንም ማስረጃ እንደሌላቸውና ጭራሽ ኖሮበት በማያውቀው የኒው ዮርክ አካባቢ የቡድኑ አባል ነው ብለው እንደወነጀሉት ተናግረዋል።
የኤልሳልቫዶር ፕሬዘደንት ግን ግለሰቡን ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል። ይህም የኪልማርን ቤተሰቦችና ደጋፊዎች ወደሌላ ችሎት ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሬዘደንት ቡኬሌ ወ ዋሽንግተን ዲሲ መምጣት አስታከው የሜሪላንድ ሴናተር ክሪስ ቫን ሀለን ከፕሬዘደንት ቡኬሌ ጋር ለመነጋገር በደብዳቤ ጠይቀዋል።

ከሁለቱ መሪዎች ጋዜጣዊ መግለጫ በኋላም ለጋዜጠኞች መልስ ሰተዋል።