
በቀን በአማካይ እስከ 95 ሺህ መኪኖችን የሚያስተናግደውና በዲሲና በቨርጂንያ ማዕከላዊ መገናኛ በመሆን የሚያገለግለው የቲዎዶር ሩዝቬልት ድልድይ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ 127 ሚልየን ዶላር የሚያወጣ መሰረታዊ ጥገና ሊደረግለት እንደሆነ ተነግሯል።
ይህን ፕሮጀክት በዋናነት የሚያስተዳደረው የዲሲ ትራንስፖርት ዲፓርትመንት ሲሆን ፕሮጀክቱ 4 ዓመት ይፈጃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተነግሯል።
ይህ ፕሮግራም ሲጀመር በድልድዩ በስተሰሜን ላይ የነበረው መረማመጃ የሚሰፋ ሲሆን ይህም ለዕግረኞችና ለባለ ሳይክሎች ተጨማሪ ቦታ ይሰጣል ተብሏል። በተጨማሪም የትራፊክ መቆጣጠሪያዎችና ምልክቶች የሚደረጉ እንደሚሆን በመግለጫው ተነግሯል።
የዲሲ ትራንስፖርት ዲፓርትመንት ይህ ጥገና የድልድዩን እድሜ ከግምት በማስገባት ወሳኝ እንደሆነ ተናግሯል። ይህ ጥገና በሚከናወንባቸው 4 አመታትም አሽከርካሪዎች ሊስተጓጎሉ እንደሚችል የተነገረ ሲሆን የመንገድ መዘጋት፤ የመስመር መዘጋትና የመሳሰሉት ሊኖሩ እንደሚችሉና ሀይዌይ 66ና በአካባቢው ላይ ባሉ መንገዶችም የትራፊክ መጨናነቅ ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል።
በዚህ ወቅትም አሽከርካሪዎች የህዝብ ትራንስፖርት እንዲጠቀሙ እንደሚመከር አስታውቀዋል። የዚህን የድልድይ ጥገና ወጪ 90 ከመቶው በፌደራል መንግስቱ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው 10% ደሞ በዲሲ መንግስት እንደሚሸፈን ተነግሯል።