
ይህ የያዝነው የግንቦት ወር በአዕምሮ ጤና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ነው። ወሩን ምክንያት በማድረግ ከተመሰረተ ሁለት ዓመታት ያለፉት የቢያ በላይነህ የአዕምሮ ጤና ፋውንዴሽን፤ የሁለት ማይል(3.2ኪ.ሜ) የግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ አዘጋጅቷል።
በጎርጎርሳውያኑ በ2021 የተቋቋመው የቢያ በላይነህ የአእምሮ ጤና ፋውንዴሽን፤ ከስኪዞፈሪንያ ፣ ባይፖላር በሽታ እና ከተለያዩ የመድሃኒት አጠቃቀም ችግር ምክንያት ህይወቱ ያለፈው የወጣቱ ቢያ በላይነህ መታሰቢያ ነው። ቢያ እና ቤተሰቡ የህክምናውን ሂደት ለመረዳት እና መፍትሄ ለማግኘት ሲሞክሩ ከ15 ዓመታት በላይ ቢጥሩም ያለመታደል ሆኖ የቢያ ህይወት ሊያልፍ ችሏል። ቢያ ከመታመሙ በፊት በነበረው የልጅነት ወቅቱ በትምህርቱ፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና በማኅበራዊ ህይወቱ የላቀ እንደነበር የሚያውቁት ይመሰክራሉ።
የቢያ በላይነህ ወላጅ እናት ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው፣ የቢያ ወላጅ አባት ቦጋለ በላይነህ፣ ወንድሙ መሳይ በላይነህ እና የቅርብ ዘመዶቹ እና ወዳጆቹ እ.ኤ.አ በ2023፤ በኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ቤተሰቦች ዘንድ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ንግግር እንዲጀመር፣ ግንዛቤ እንዲፈጠር፣ የተለያዩ መረጃዎች በቀላሉ እንዲገኙ ለማገዝ የቢያ በላይነህ የአእምሮ ጤና ፋውንዴሽን መስርተዋል።
የተቋሙ ድረገጽ የፋውንዴሽኑ ዓላማ፤ ህብረተሰቡ የአዕምሮ ህመምን ጤና ችግርን ምንነት እንዲገነዘብ፣ የተሟላ የአዕምሮ ጤና እንክብካቤ እና የድጋፍ አገልግሎቶችን ማግኘት እንዲችል ለማገዝ ባለፉት ዓመታት ወላጆቹ እና ወዳጆቹ ያሰባሰቧቸውን እውቀቶች፣ መረጃዎች እና ልምዶች የሚያጋሩበት መሆኑ ያመላክታል።
የፋውንዴሽኑ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትዝታ በላቸው (ጋዜጠኛ) ፋውንዴሽኑ እ.ኤ.አ ቅዳሜ ግንቦት (ሜይ) 17 ቀን፤ በ900 Jessup Blair Drive Silver Spring, MD 20910 ከጠዋቱ 10 ሰዓት ጀምሮ የሚከናወን የእግር ጉዞ ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል። የእግር ጉዞው ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ሲሆን፤ መሪ ቃሉም “Habeshas for mental health walk” በግርድፍ ትርጉሙ “ሀበሾች ለአዕምሮ ጤና” ይሰኛል።
በመርሃግብሩ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ይህን ሊንክ በመጫን በነጻ እንዲመዘገቡ እንዲሁም በእለቱ በስፍራው እንዲገኙ ጋብዘዋል።