
በመዥገር የሚተላለፉ በሽታዎች በክልላችን በፍጥነት እየተስፋፉ ነው። ለዚህ ደሞ እንደ ምክንያት የተጠቀሱት የአየር ንብረት መሞቅ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች መበራከትና እና የመዥገሮች ቁጥር መጨመር ናቸው፡፡ ይህንን ተከትሎም በመዥገር የሚተላለፉ እንደ ላይም ዲዚዝ (የላይም በሽታ) እና ሌሎች ኢንፌክሽኖች በሜሪላንድ፣ ቨርጂኒያ እና ዋሽንግተን ዲሲ በብዛት እንዲታዩ ምክንያት ሆነዋል።
የላይም በሽታ በአካባቢያችን እጅግ የተበራከተ ሆኗል፡፡ ይህ በሽታ ከሰው ወደሰው ለመተላለፍ ብዙውን ጊዜ የድኩላ መዥገር ተብለው በሚጠሩት ጥቁር እግር ያላቸው መዥገሮች ላይ በመኖር መዥገሮቹ ሰውን ሲነክሱ በንክሻ ይተላለፋል። የላይም በሽታ ምልክቶቹ ትኩሳት፣ ድካም፣ የመገጣጠሚያ ህመም እና የኢላማ መለማመጃ ክቦች የሚመስል ቀይ ሽፍታን ያካትታሉ።ይህ ህመም በጊዜ ካልተደረሰበትና በጊዜ ካልታከመ ከባድ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። በቨርጂኒያና ሜሪላንድ የላይም (Lyme) በሽታ ከተስፋፋባቸው የአሜሪካ ካሉ ግዛቶች ውስጥ ይገኙበታል። የላይም በሽታ በጊዜ ካልታከመ የመገጣጠሚያ ህመም፤ የነርቭ ችግር፤ የመዘንጋት ችግር፤ የልብ ችግር እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ድካም ያስከትላል፡፡ አለፍ ሲልም ግማሽ ፊትን ፓራላይዝ ያደርጋል፡፡

ሌላኛውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከተ የመጣው ደሞ ባቤሲዮሲስ የሚባል ሌላ በሽታ ነው። ይህ በሽታ ልክ እንደ ወባ የሚሰራ ሲሆን ለአረጋውያን ወይም ደካማ የሰውነት የመከላከል አቅም ላላቸው ሰዎች በጣም አደገኛ ሊሆን ይችላል። በ2025 የተደረገ አዲስ ጥናት ጥገኛ ተህዋሲው በዲኤምቪ ውስጥ በሚገኙ የአካባቢ መዥገሮች ውስጥ መገኘቱን የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚያ መዥገሮች ውስጥ ብዙዎቹ የላይም በሽታንም ይይዛሉ።
ይህን የበሽታ መስፋፋት ከግምት በማስገባትም የጤና ባለሞያዎች ለሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል፡፡ በሳር በተሸፈኑ አካባቢዎች ረጅም ልብስ መልበስን፣ የትንኝ መከላከያ መጠቀምን እና ከቤት ውጭ ከቆዩ በኋላ እራስዎን እና ልጆችዎን በመዥገር መነከስዎን ወይም አለመነከስዎን እንዲፈትሹ የሚመከር ሲሆን መዥገር ከነከሰዎት በኋላ ህመም ከተሰማዎት ወዲያውኑ የሕክምና እርዳታ እንዲያገኙም ይመከራሉ፡፡ እነዚህን በሽታዎች ቀድመው ማከም የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል።