
በ2025፣ በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚመሩትና በኮንግረስ ያሉ ሪፐብሊካኖች “አንድ ትልቅ ቆንጅዬ ህግ” የሚባል ሁሉን አቀፍ የሆነ ረቂቅ ህግ አቅርበዋል። በዚህ ረቂቅ ህግ ታዲያ የታክስ ጉዳዮች ላይ፣ የድንበር ደህንነትን እና የኢሚግሬሽን ለውጦችን ያካትታል።
ከነዚህም አንዱና ትልቅ ለውጥ የታየበት የረቂቁ አካል ደሞ የስደተኞች አገልግሎቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሚሰበሰበው ገንዘብ ስደተኞችን ዲፖርት ማድረግ፤ እስር ቤት ማቆየት፤ የደቡባዊ ድንበር አጥር ግንባታን ማስቀጠልና የመሳሰሉ ይገኙበታል። እነዚህ ክፍያዎች ሰዎች ወደ አሜሪካ በማንኛውም መንገድ ለመምጣት ወይም ለመቆየት እንዳይችሉ ወይንም እንዲከብዳቸው የሚያደርግ እንደሆነም በሪፐብሊካን የህጉ አርቃቂዎች ታምኖበታል።
አዲስ ክፍያዎች
- የጥገኝነት ጠያቂዎች: ከዚህ ቀደም በነጻ የነበረው የአሳይለም ማመልከቻ በዚህ ረቂቅ ህግ መሰረት በአመልካች አንድ ሺህ ዶላር እንዲያስከፍል ተደንግጓል። በተጨማሪም ለስራ ፍቃድ ማመልከቻ ወይንም ማሳደሻ በየ6 ወሩ 550 ዶላር ክፍያን እንዲከፈል ያዛል። ጉዳያቸው እስኪታይላቸው የሚጠብቁ ደሞ በየአመቱ መቶ ዶላር እንዲከፍሉ ያዛል። ለአምስት አመት ጉዳዩን የሚጠባበቅ ሰው በአማካይ እስከ 7000 ዶላር ይከፍላል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል።
- ሌሎች ፕሮግራሞች: የሰብአዊ ፓሮል $1,000 ያስከፍላል። ጊዜያዊ የተጠበቀ ሁኔታ (TPS) ለማመልከት ቀድሞ ከነበረው $50 ዶላር ወደ $500 እንዲል ተጠይቋል። )
- ቅጣቶች: ድንበርን በህገ-ወጥ መንገድ መሻገር ከ250 ዶአልር ወደ $5,000 እከፍ እንዲል ተጠይቋል።
- ወደ ሀገር ቤት ከሚላክ ገንዘብ ላይ ታክስ፡ በተጨማሪም ወደ ውጭ ሀገር ከሚላክ ገንዘብ ላይ የ5% ቀረጥ እንዲጣል ያዛል።
- የሥራ ፈቃድ ክፍያ: ይህ ህግ ተግባራዊ ከሆነ የጥገኝነት ጠያቂዎች፣ በፓሮል የገቡ እና TPS ያላቸው ሰዎች ለሥራ ፈቃድ እና ለማደስ በየ6 ወሩ $550 እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸዋል። የስራ ፈቃዳቸው የ2 አመትም ይሁን የ5 አመት በየ6 ወሩ ይህን $550 ዶላር ካልከፈሉ የስራ ፈቃዳቸው ዋጋ አይኖረውም።
ይህ ምን ያስከትላል?
ለማመልከት አስቸጋሪ ይሆናል: እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ክፍያዎች ድሃ ስደተኞች ጥገኝነት ወይም ሌላ ጥበቃ ለመጠየቅ እንዲቸገሩ ከማድረግ አልፎ የተወሰኑትን ያላቸውን ህጋዊነት እንዲያጡና እንዲባረሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል። አንዳንዶች ታዲያ ይህ አካሄድ የአለም አቀፍ የስደተኞችን ህግ ይጥሳል ቢሉም የትራምፕ አስተዳደር ከአብዛኞቹ አለም አቀፍ ተቋማት ራሱን በማግለሉ ይህ እንደ ችግር የሚያየው አይሆንም።
የገንዘብ ችግሮች: ገንዘብ ወደ አገር ቤት የሚልኩ ሰዎች ወይንም ወደሌላ አገር የሚልኩ ሰዎች ተጨማሪ ግብር የሚከፍሉ ይሆናል በተለይም ጉዳያቸው ያላለቀላቸው ሰዎች ከሆኑ በወጪ ላይ ወጪ የመሆን እድላቸው ትልቅ ይሆናል። ይህም ወደ ባሰ ድህነት ሊከታቸው ይችላል።
ተጨማሪ ፖሊሶችና ማጎሪያዎች: ከዚህ የሚሰበሰቡ ገንዘቦች የኢሚግሬሽን ፖሊሶችን ለመቅጠርና የስደተኛ ማጎሪያዎች ክፍያን ለመፈጸም ይውላሉ። ሆኖም ተቺዎች የዚህን አካሄድ ፍትኃዊነት ላይ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ።
ኮንግረስ እስካሁን በዚህ ረቂቅ ህግ ላይ አልተስማማም። አንዳንዶች ህጋዊ ኢሚግሬሽንን ያግዳል ሲሉ ሌሎች ደግሞ ለአገር ደህንነት አስፈላጊ ነው ይላሉ። ይህ ህግ ከጸደቀ ከስደተኞች በግብር ከሚሰበሰበው በተጨማሪ በጠቅላላው በአመት በግምት የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከአሳይለምና የስራ ፍቃድ እስከ 1.5 ቢልየን፤ ከቲፒኤስና ፓሮል እስከ 400 ሚልየን፤ ስደተኖችን ስፖንሰር ከሚያደርጉ ቤተሰቦች ከሚሰበሰብ ክፍያ እስከ 85 ሚልየን፤ በቦርደር ሲገቡ ከሚያዙ ሰዎች ቅጣት እስከ 12 ቢልየን እንዲሁም ወደ ውጭ ሀገር ከሚላኩ ገንዘቦች ከሚሰበሰብ ግብር እስከ 4 ቢልየን ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚገመት ተነግሯል።