
የዲሲ ምክርቤት ሊቀ መንበር በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የቀደመውና አሮጌውን አር.ኤፍ.ኬ ስታዲየምን ወደ አዲሱ የኮማንደርስ የስፖርት ቡድን ስታዲየምነት ለመቀየር የታቀደውን ግንባታ ምክርቤቱ እንደሚያጸድቀው አመላክተዋል። የስታዲየሙ ግንባታ በተለይም ከኮቪድ 19 በኋላ የኢኮኖሚ መንገዳገድ እየገጠማት ላለው ዋሺንግተን ዲሲ፤ ትልቅ የቱሪዝም እና የንግድ መነቃቃት ዕድልን ይፈጥራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ሊቀመንበሩ ይኸንን ያሉት ትላንት ሃሙስ መሆኑን የሀገር ወስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሊቀመንበሩ ከደብሊው.ቲ.ኦ.ፒ ጋር በልዩ ሁኔታ ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ ከተማዋ የግብር ከፋዮችን ገንዘብ ለስታዲየሙ ግንባታ በድጎማነት መጠቀም የለባትም በሚለው ተነስቶ የነበረው አለመግባባት በመልካም ውይይት እንዲፈታ እንደሚሰሩ ለጣቢያው መግለጻቸው ሰፍሯል።
የዲሲ ከንቲባ ጽ/ቤት ከግዙፉ የአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን ኮማንደርስ ክለብ ጋር ባደረገው ውል መሰረት፣ ቡድኑ ለስታዲየሙ ግንባታ 2.7 ቢሊየን ዶላር የሚያዋጣ ሲሆን፤ በአንጻሩ የዲሲ አስተዳደር በስታዲየሙ ዙሪያ የሚገነቡ መኖርያቤቶች፣ የስፖርት መዝናኛዎች እና ሱቆች ግንባታ 1.1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያወጣ ይጠበቃል።
ከሰሞኑ ም/ቤቱ ከዲሲ ወረዳ ሰባት ዜጎች ጋር ግንባታውን በተመለከተ ውይይት ማካሄዱ የተመለከተ ሲሆን፤ በውይይቱ የተሳተፉ በርካታ ነዋሪዎች ግንባታውን በተመለክተ ቅሬታ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር።